መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ለማስተማር ፍቃደኛ የማይሆኑ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ስለመኖራቸው ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር አስታውቋል፡፡

"በዓለም አቀፍ ደረጃ 300 ሚሊየን እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ5 ሚሊየን በላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች እንደሚገኙ ይገመታል" ያሉት የማኅበሩ ፕሬዝደንት ማህሌት ንጉሴ፤ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚገኙ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች ለአድሎ እና ለመገለል ተጋላጭ ሲሆኑ እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለ ዳውንሲንድረም እንዲሁም እንደ አጠቃላይ የአእምሮ ህመም በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በትምህርት፣ በሥራ፣ በማኅበራዊ ሕይወት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ናቸው ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

በክልሎች ላይ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶች ተደራሽ አለመሆኑን የተናሩት ፕሬዝደንቷ፤ በአዲስ አበባ ከተማ 22 የሚሆኑ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶች ስለመኖራቸውም አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በርካታ ችግሩ ያለባቸው ሕጻናት እድሜያቸው በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዳያልፍ ምክንያት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

አክለውም በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ለማስተማር ፍቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ ስለመኖሩ የገለጹ ሲሆን፤ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ በአንጻሩ መሻሻሎች ቢኖሩም የክፍያ ዋጋው ግን የሁሉንም የማኅበረሰብ አቅምን ያገናዘበ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌሎች ሀገራት ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በትምህርት ስርዓት ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ እንደሚስተዋል በመግለጽም፤ ማህበሩ ለአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ዜጎች የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት እና የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማሟላት ውጤታማ ሥራዎች መሰራት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

አእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በማንኛውም ጉዳይ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በቅድሚያ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ሊታረም እንደሚገባም የማኅበሩ ፕሬዝደንት ማህሌት ንጉሴ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የትምሀርት ስርዓት ሂደቱ ላይ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ "ትኩረት በመስጠት በትምህርት ስርዓት ሂደት ላይ እንዲሳተፉ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይገባል" ተብሏል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ የአእምሮ እድገት ውስንነት ቀን መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

ቀኑም "የድጋፍ ስርዓቶቻችን እናሻሽል" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተነግሯል፡፡

ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ባለባቸዉ ሕጻናት ወላጆች በ1987 ዓ.ም. የተቋቋመ ሀገር በቀል ማኅበር ሲሆን፤ በ9 ክልሎች እና በ18 ከተሞች ላይ ተደራሽ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ነግር ግን አሁንም በጋንቤላ፣ በቤንሻንጉል እና በአፋር ክልሎች ላይ ማህበሩ ተደራሽ አለመሆኑን ፕሬዝደንቷ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

አክለውም ዋና ዓላማው የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች በሙያና በቴክኒክ ስልጠና መደገፍ እንዲሁም ተዛማጅ እገዛዎችን በማድረግ፤ ዜጎቹን እና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ ማድረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ