መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ኦ-ኔጌቲቭ የደም አይነት ኑሮት ደም የሚለግስ ሰው ቁጥር አሁንም ድረስ እጅግ አነስተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታውቋል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ኦ-ኔጌቲቭ (O Negative) ያላቸው ሰዎች ከሌሎች የደም አይነቶች በተለየ መልኩ ለሁሉም ሰው የሚሆን ደም ያላቸው በመሆኑ፤ ወደ ሕክምና ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት ምርመራ ሳይደረግም ሊሰጥ እንደሚችል ለአሐዱ ተናግረዋል።

አክለውም ኦ- ኔጌቲቭ የሚቀበለው ከራሱ ተመሳሳይ የደም አይነት ካለው ጋር በመሆኑ እና የደም አይነቱ ያላቸው ሰዎችና የለጋሾች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ፤ የዚህ ደም አይነት ያላቸው ሰዎች በሚታመሙበት ወቅትና ደም በሚያስፈልጋቸው ሰዓት እጥረት እንደሚያጋጥም አስረድተዋል።

በተመሳሳይም ኤቢ (AB) የሚባለው የደም አይነት ለጋሽ ቁጥርም አነስተኛ የሚሆንበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሌላ በኩል አብዛኛው 40 በመቶ ያክል የሚሆነው ደም የሚለግስ ሰው ኦ-ፕላስ የደም አይነት እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም የኦ-ኔጌቲቭ ደም አይነት ያላቸው ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ የቡድን ገጾችን በመክፈት መረጃዎችን በመለዋወጥ እንዲለግሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ይህ አይነት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

"የደም ፍላጎት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ስላለ ሁሉም ሰው ልገሳውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት" ያሉት ም/ ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም የኦ-ኔጌቲቭ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ችግሩን ለመቅረፍ መለገስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ