መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ምክንያት ከዚህ ቀደም በበረሃማ አካባቢዎች የሚታወቁ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች፤ በአዲስ አበባ ከተማ የመከሰት ዕድል እንዳላቸው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ የአየር ንብረት ለውጥ እና አማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ሰዒድ አብደላ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ እና የሙቀት መጨመር በአዲስ አበባ ከተማም እየተስተዋለ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተሽከርካሪዎች በሚለቀቅ ካርቦን ሞኖክሳይድ ጋዝ፣ ከብስባሽ ቆሻሻ በሚለቀቅ ሚቴን ጋዝ፣ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ከሚውሉ የከሰል እና የማገዶ እንጨቶች የሚወጣ ጭስ፣ እና ከፋብሪካዎች በሚለቀቅ በካይ ጋዝ አማካኝነት የሚደርስባት የአየር ብክለት እየጨመረ መምጣቱንም ነው የገለጹት፡፡

አክለውም "ተስማሚ የነበረ አየር መቀየርን ጨምሮ በከተማዋ በቅርብ ርቀት የወባ በሽታ መከሰት ምልክቶች የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህም ብክለት በጊዜ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ በከተማዋ ከዚህ በፊት ያልተለመዱ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራው የሚገኘው የማንቃት ሥራ በቴክኖሎጂ አቅርቦት እጥረት እና ሌሎችም ምክንያቶች የእቅዱን ያህል ማከናወን እንዳልቻለም ዳይሬክተሩ አክለው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ