መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በቸልተኝነት በፈጸሙት የሕክምና ስህተት ምክንያት ሕሙማንን ለሞት፣ ለከፋ አደጋ ከዚህም አለፍ ሲል ለተለያዩ በሽታዎች ያጋለጡ 41 የጤና ባለሞያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል።
ከተፈጸሙ ስህተቶች ውስጥም፤ ከቀላል እስከ ከፍተኛ ቀዶ ጥገና መደረግ ያልነበረባቸው ታካሚዎችን የሕክምና አገልገሎቱን የሰጡና ምንነታቸው የማይታወቅ መድኃኒቶችን ያለአግባብ በመርፌ መልክ የሰጡ ባለሙያዎች ላይ የሙያ ፍቃድ ስረዛ እርምጃ መውሰዱን በባለስልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር ገልገሎ ኦልጅራ ለአሐዱ ተናገረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በዋናነት ስህተቶቹ የሚፈጸሙት የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ የሕክምና አገልግሎት በመስጠትና በቸልተኝነት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም በመሆኑ ታካሚዎች ለሞት፣ ለከፋ አደጋና ለተጓዳኝ በሽታዎች ተጋልጠዋል ብለዋል።
በተደጋጋሚ ከሚስተዋሉ ስህተቶች ውስጥም አላስፈላጊ ቀዶ ጥገና ማድረግና ያለአግባብ የሰውነት ክፍሎች ላይ መድኃኒቶችን በመርፌ መልክ መሰጠት እንደሆነ ገልጸዋል።
በተወሰደው እርምጃዎች መሠረትም፤ ዳግም ወደ ሙያው እንዳይመለሱ እንዲሁም የትምህርት ማዕረጋቸው እንዲነጠቅ መደረጉን አንስተው፤ "በ41ዱ ባለሙያዎች ላይ እርምጃው የተወሰደው ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ነው" ብለዋል።
"የችግሩ ገፈት ቀማሾች ለባለሥልጣኑ ቅሬታዎችን ካቀረቡ ወዲህ፤ በተለያዩ የሕክምና ሙያ ዘርፎች አማካኝነት በተወጣጡ ባለሙያዎች ግምገማ ከተደረጋ በኋላ እርምጃዎች ተወስዷል" ሲሉም አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ በከተማዋ የችግሩን መንሰራፋት ከአቤቱታ አቅራቢዎች በመረዳት በተለየ መልኩ መሰል እርምጃዎች እና የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ባለሙያዎችም የሙያ ሥነ-ምግባራቸውን እንዲያከብሩና ነዋሪውም መሰል ድርጊቶችን ሲያስተውል ጥቆማዎችን በመሰጠት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በወልደሐዋርያት ዘነበ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በቸልተኝነት የሕክምና ስህተት የፈጸሙ 41 የጤና ባለሙያዎች የሙያ ፈቃድ መሰረዙ ተገለጸ
