ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በየጊዜው የነዳጅ እጥረት ከመሻሻል ይልቅ እየተባሰ በመምጣቱ፤ ሽያጩ በኩፖን እንዲሆን መወሰኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው በኩል ለሁሉም ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ በተሰራጨው ሰልኩላር ደብዳቤ መሰረት ከጥር 30 ጀምሮ ሁሉም የነዳጅ ማደያ ያለባቸው ከተሞች ነዳጅ በኩፖን እንዲሸጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የነዳጅ ምርት እጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተለይ የባለ ሁለት እግር ሞተሮች በየቀኑ ተመላልሶ መቅዳት ለኮንትሮባንድ ሽያጭ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን ቢሮው ገልጿል።
በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች የኩፖን ሥርዓት በመዘርጋቱ ሥርጭት ላይ ያለውን የቤንዚን ምርት በአግባቡ ማሰራጨት መቻሉን የገለጸው የክልሉ ንግድ ቢሮ፤ ለክትትልም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ማስተዋሉንም በደብዳቤው አመላክቷል።
በዚህም መሰረት የነዳጅ ማደያ ያለባቸው ከተሞች ከጥር 30/2017 ዓ.ም ጀምሮ የትኛውም ተሽከርካሪ በኩፖን ብቻ እንዲስተናገድ እና ታርጋ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች ሀጋዊ የተሽከርካሪ ሠሌዳ እስኪያወጡ ድረስ የግልም ሆነ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች እንዳይስተናገዱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከዚህ በተጨማሪም የነዳጅ ምርት ሽያጭ በኤሌክትሮኒክስ (በቴሌ ብር እና ሲቢኢ ብር) የመገበያያ መንገዶች ብቻ እንዲፈጸም አሳስቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ