መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ከአቅም በላይ የሆነ አደጋ ሲያጋጥም አስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንዲታወጅ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 20ኛ መደበኛ ስብሰባውን በትናንትናው ዕለት አካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ያደረገ ሲሆን፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም መንግሥት ማንኛውም ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋ በዜጎች ላይ እንዳይደርስ የማድረግ ሥራ የመስራት ዋናኛ ተልዕኮው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳት ሲደርስም ተጎጂዎችን የሰብዓዊ ድጋፍ በጊዜ እንዲደርስ የማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ዘርፍን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሰበትን ሁኔታ የተላበሰ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር የቅድመ አደጋ ወቅት እና የድህረ አደጋ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የፌደራል እና የክልል አደጋ መካከል ሥራ ውስጥ አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ በዋናነት ከአቅም በላይ የሆኑ አደጋዎች ሲኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑንም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ እና የዘላቂ ድጋፍ የሰላም ግንባታ ዕቅዶችን ለማስተሳሰር በሚያስችል መልኩ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱንም ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡
ረቅቅ አዋጁ ሰባት ክፍሎችና አርባ አንቀፃችን የያዘ ሲሆን፤ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤትን የማቋቋም ስልጣን ለኮሚሽኑም የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመንግሥት ዋና ተጠሪውን አጠር ያለ ማብራሪ ያደመጡት የምክር ቤቱ በአባላት ረቂቅ አዋጁ ላይ ቢካተት ያሉትን አንስተዋል፡፡
በዚህም ከተነሱ ሀሳቦች መካከል በተለይም በክልል አደጋ ስጋት ላይ በርካታ ሥራ የሚሰራው በተቋማት በጎ ፍቃድ በመሆኑ፤ በተለይ ችግር በተደጋጋሚ ለሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ይህ አዋጅ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተነስቷል፡፡
የተነሱት አብዛኛው ድጋፍ በመሆናቸውም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ሲል አጽድቆታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ