ከዚህ በፊት የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ አማፂ ቡድኑን ለመደምሰስ ሃሳብ እንዳላቸው ሲገልጹ እንደነበር ተነግሯል፡፡
አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያውያን ተፈናቅለው በተሠሩ ድንኳኖች ውስጥ የሚኖሩባት በቱርክ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ኢድሊብ የሶሪያ መንግሥት ጥቃት መፈጸሙን በቦታው የነበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህም የአማፂያኑ ጦር አሌፖን ተቆጣጥረው በምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ በኩል ሐማ ወደ ተባለች ከተማ ሲገሰግሱ፤ ሶርያ እና ሩሲያ ከፍተኛ የአየር ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ተገልጿል።
የሶሪያ መንግሥት ሚዲያ እና የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢዎች የሩስያ እና የሶሪያ ተዋጊ ጄቶች በሰሜናዊ ምዕራብ ሶሪያ በአማፂያን በተያዙ ቦታዎች ላይ ኢላማዎችን እየመቱ መሆናቸውን ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው የተቃዋሚዎች የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ተከታታይ ቡድን፤ ጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎች እና ተዋጊዎች ተገድለዋል ብሏል።
የሩሲያ እና የኢራን ባለስልጣናት በበኩላቸው ትናንት ሰኞ በሰጧቸው መግለጫዎች፤ ከፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጎን በመቆም ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ዕርዳታዎችን ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ላለፉት አስርት ዓመታት የቀጠለ ሲሆን፤ የአሳድ መንግሥት እና አጋሩ ሩሲያ በጋራ አማጺያኑን እየተፋለሙ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ የሶርያ አማጽያን በበሽር አል አሳድ መንግሥት ላይ የከፈቱት ጥቃት ተከትሎ፤ እንደ አዲስ በሀገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ስጋት ተፈጥሯል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ገይር ፔደርሰን እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት በአስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ሳምንት እንደአዲስ ያገረሸውና እስካሁን እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ጦርነት፤ በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ሞት፣ ጉዳትና መፈናቀልን ማስከተሉም ተገልጿል፡፡
በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ቢያንስ 25 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ
ሕዳር 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሩስያ እና የአሳድ መንግሥት ተዋጊ ጄቶች በሰሜን ሶሪያ በአማፂያኑ ቁጥጥር ሥር በምትገኘው ኢድሊብ ከተማ በፈጸሙት ጥቃት 25 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡