ሕዳር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ዓደዋ ከተማ በታዳጊ ማህሌት ተክላይ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀመው አንደኛ ተከሳሽ ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ ተሰጥቷል።

በትግራይ ክልል የመቀሌ ከተማ መካከለኛ ፍርድ ቤት በታዳጊ ማህሌት ተክላይ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች ላይ ዛሬ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የ16 ዓመት ታዳጊዋ የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ማህሌት ተክላይ መጋቢት 10 ቀን 2016 ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ከነበረበት ታግታ ተወስዳ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ ተገድላ መገኘቷ ይታወሳል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ አንገቷን አንቆ በመያዝ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ በባጃጅ አግቶ በመውሰድ ለ30 ደቂቃ ያክል በጫማ ማሰሪያ ገመድ አሰቃይተው እንደገደሏት የመቀሌ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

አንደኛ ተከሳሽ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ ወደ ሥራ እንደገባ፤ ገድለው ከቀበሯት ከሦስት ቀናት በኋላም አባቷ ተክላይ ግርማይን 3 ሚሊየን ብር እንደጠየቀው ተገልጿል።

ሁለተኛ ተከሳሽም ከአንደኛ ተከሳሽ እኩል የወንጀሉ ተባባሪ መሆኑን ያስረዳው ዐቃቤ ሕግ፤ ይህ የግድያ ወንጀል ጭካኔ የተሞላበት በመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን በማረጋገጥ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል።

በዚህም ታዳጊዋ ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀመው 1ኛ ተከሳሽ በሞት፣ 2ኛ ተከሳሾች ደግሞ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።