መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አር ኤስ ኤፍ) በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሚገኘው የሪፐብሊካን ቤተ-መንግሥት ላይ ባደረሰው የድሮን ጥቃት ሦስት ጋዜጠኖች መገደላቸው ተገልጿል፡፡

በጀነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሠራዊት (ኤስ ኤ ኤፍ) ፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግሥቱን ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ከሚመሩት በፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አር ኤስ ኤፍ) እጅ በማስለቀቅ በዛሬው ዕለት በቁጥጥሩ ሥራ ማስገባቱን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ፤ ከሰዓታት በኋላ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በከፈተውና በቤተ-መንግሥቱ ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ እና የሚዲያ ስብስብ አዳራሽ ላይ ባነጣጠረ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት 3 ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገልጿል፡፡

ጋዜጠኞች በቤተ-መንግሥቱ ተገኝተው ለሱዳን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲዘግቡ በነበሩበት ወቅት በጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑም የሱዳን ጦር ምንጮች ለኤፍ ፒ ገልጸዋል፡፡

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቤተ-መንግሥቱን ጨምሮ የሱዳን በርካታ አካባቢዎችን ለበርካታ ጊዜያት ተቆጣጥሮ የቆየ ሲሆን፤ የሱዳን ጦር ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግሥቱን መልሶ በመቆጣጠሩ ወሳኝ የተባለን ድል መቀዳጀቱ ተነግሯል።

ነገር ግን አሁን ላይ ፈጥኖ ደራሹ ኃይሉ በቤተ-መንግሥቱ ጥቃት ከማድረሱ በተጨማሪ፤ አሁንም የካርቱም ደቡባዊ ክፍልን እና የካርቱም ተጎራባች በሆነችውን ኦምዱርማን ከተማ መካከል ያሉ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል።

በእዮብ ውብነህ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ