መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) እስከ አሁን ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ተጨማሪ ክፍያን የሚያስከትለው ረቂቅ አዋጅ መቅረቡ ሠራተኞች ላይ ሌላ የኑሮ ጫናን የሚፈጥር ነው ሲል የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) አስታውቋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በቅድመ አደጋ፣ በአደጋና በድህረ አደጋ ወቅቶች ለሚወሰዱ የአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ምላሽና መልሶ ማቋቋም የሚሆን፤ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መቋቋሙ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት ሌሎች ጉዳዮችንም አካትቶ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች ከደመወዛቸው ላይ ተቆራጭ በማድረግ፤ ለአደጋ ስጋት የሚሆን ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ላይ አባላቱ ከተወያዩበት በኋላ ለምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ተመላክቷል።
አሐዱም "ይህንን ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እንዴት ይመለከተዋል?" ሲል ጠይቋል።
የኮንፌዴሬሽኑ የውጪና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አያሌው አህመድ በሰጡት ምላሽ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጊዜ ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ "ተጨማሪ ክፍያን የሚጠይቀው ረቂቅ አዋጅ መቅረቡ ሠራተኞች ላይ ሌላ ጫናን የሚፈጥር ነው" ብለዋል።
በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ ገና ስላልጸደቀ 'ሕግ ሆኖ ይወጣል ወይስ አይወጣም' የሚለውን በተመለከተ የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አስቀድሞ የሚወያይበት ጉዳይ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
አክለውም በተደጋጋሚ ጥያቄ ከተነሳበት የሠራተኞች መብት ጥያቄዎች አንዱ፤ 'ከደመወዝ ላይ የሚቆረጠው የታክስ መጠን አሁን ያለውን የኑሮ ውድነትና ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መሻሻል አለበት' የሚል እንደሆነ አስታውሰዋል።
ቀድሞ በተቀመጠው ሕግ መሠረትም እስከ 600 ብር ድረስ ከታክስ ነፃ መሆኑን የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ ደሞዙ ከ600 ብር በላይ የሆነ ሰው በየደረጃው የታክስ ክፍያ መጠን መቀመጡን አንስተዋል።
ይህ ሕግም ቀድሞ በነበረው የዝቅተኛ ደሞዝ የተሰላ ስለነበረ ጥያቄው በድጋሚ መሻሻል እንዳለበት የሚገልጽ መሆኑን፤ የውጪና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊው ለአሐዱ ተናግረዋል።
ኢሰማኮ በጉዳዩ ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥናት ተድርጎ እርምጃ እንዲወስድበት ለማስቻል በተደጋጋሚ ቢቀርብም፤ እስካሁን ግን በመንግሥት በኩል ይፋዊ የሆነ ምላሽ እንዳልተሰጠው የገለጹም ሲሆን፤ ትኩረት እንዲሰጥበት አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ተጨማሪ ክፍያን የሚጠይቀው ረቂቅ መቅረቡ ሌላ ጫናን ይፈጥራል ተባለ
