መጋቢት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሆን ብለው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የደንብ ልብስ መለያን አስመስለው በመልበስ ማስታወቂያ የሰሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሸጋው ጫኔ አንለይ፣ መሀመድ ሀምዛ ያሲን፣ አቤኔዘር ተስፋዬ በየነ እና ጌትነት ደምለው ዳምጤ የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ደብረወርቅ ሕንፃ አካባቢ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የቀድሞ የደምብ ልብስ የሚመስል በማሰፋት በጎዳና ንግድ ላይ የሚተዳደሩትን ግለሰቦች ንብረት በመበተንና በመደብደብ የቢሮውን ገፅታ በሚያንቋሽሽ መልኩ የሀሰት ቪዲዮ አዘጋጀተው በቲክቶክ ማሰራጨታቸው ተገልጿል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ግለሰቦቹ በቀረበባቸው አቤቱታ መሠረት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ግለሰቦቹ በተቋሙ እና በሠራተኞቹ ላይ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ አሉታዊ ስሜት እንዲፈጠር አስበው የተቋሙን የቀድሞ የደምብ ልብስ የሚመስል አዘጋጅተው ድርጊቱን መፈጸማቸውን ፖሊስ ያስታወቀ ሲሆን፤ የፈጸሙት ድርጊት በሕግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ገልጿል፡፡

አክሎም ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት በሕግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ፤ መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ