ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቀን በአማካኝ 4 የትራፊክ አደጋዎች ይከሰቱበት የነበረው በሸገር ከተማ ባለፉት 6 ወራት በተደረገ የቁጥጥር ሥራ አደጋውን መቀነስ መቻሉን የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የሰዎች ሞት፣ ከባድ እና ቀላል አደጋዎችን እንዲሁም የንብረት ውድመት እያስከተለ የነበረውን አደጋ መቀነስ እንደተቻለ ለአሐዱ የተናገሩት የትራንስፖርት ቢሮው ኃላፊ ያሱን አህመድ ናቸው።
በሸገር ከተማ በሚደርስ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ከሚያጡ ዜጎች መካከል 70 በላይ በመቶ ያህሉ እግረኞች መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው፤ "አካባቢው የሀገሪቱ 60 በመቶ የተሸከርካሪ ፍስት የሚካሄድበት መሆኑ ለችግሩ መባባስ አንድ መንስኤ ነው" ብለዋል።
አብዛኛው አደጋዎች ምሽት ላይ እንደሚከሰቱ ታውቆ፤ ፍጥነት መገደቢያ፣ የመንገድ ዳር የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በማዘጋጀት፣ የቁጥጥር ባለሙያ አማራጮች በማብዛት፣ ከዚህ ቀደም የሚደርሱ አደጋዎች አንፃር በቀን ሁለት እና ከዚያ በላይ አደጋዎች እንደሚመዘገቡ አንስተዋል።
ኃላፊው አያይዘውም፤ "አደጋ በሚበዛባቸው ቦታዎች የምህንድስና ማሻሻያዎች ማድረግ፣ የመረጃ ሥርዓትን ማዘመንና የድህረ-አደጋ ሕክምና አሰጣጥን የማሻሻል ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል።
በቀጣይም የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት፤ ሕይወትን መታደግ የሚያስችል ሥራዎችን እንዲሠሩ አሳስበዋል።