ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክለውን መመሪያ በትናንትናው ዕለት ማገዱ ተሰምቷል፡፡

በአክሱም ከተማ የሚገኙ 5 ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው እንዳይማሩ አስተዳደራዊ እግድ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የክስ አቤቱታውን ለአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክቶ ጊዜያዊ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፤ በውሳኔውም "የክስ ክርክሩ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ቢቆይ በተማሪዎቹ ላይ የማይቀለበስ የመብት ጥሰት ሊያስከትል ስለሚችል ተማሪዎቹን ለማገድ የተላለፈው አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲታገድ" ትዕዛዝ አስተላልፏል።

Post image



ይህ እግድ የክስ ሂደቱ ውሳኔ እስከሚያገኝ ወይም ተለዋጭ ትእዛዝ እስኪሰጥ ድረስ የሚጸና መሆኑንም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት ክልከላ የተደረገባቸው ተማሪዎቹ ሂጃብ ለብሰው የመማር መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም፤ በክልከላው ምክንያት የምዝገባ ጊዜ አልፏቸው የነበሩት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገቡ ወስኗል፡፡

እንዲሁም በሂጃብ ምክንያት ተማሪዎችን ያገዱት ትምህርት ቤቶች ለጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የሙስሊም ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ከሰሞኑ በአክሱም ከተማ የሚገኙት ወራዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት፣ አብርሃ አፅብሃ፣ ቀዳማዊ ሚኒሊክ እና ክንደያ ትምህርት ቤቶች፤ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን ተከትሎ፤ ከፍተኛ ቅሬታ እና ተቃወውሞ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ ክልከላው የተጣለው፤ የትምህርት ቤቶች አደረጃጀት እና መመሪያ የተባለው ሕግ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ ሂጃብ እንዳይለብሱ በመከልከላቸው ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው እንዲሁም ለእስር እና ለእንግልት መዳረጋቸውን ተነግሯል፡፡

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እና የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአክሱም ሙስሊም ተማሪዎች መብቶች ሳይሸራረፋ እንዲከበሩ ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት "ምንም አይነት ሕጋዊ መሰረት በሌለበት የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ የማገድ ተግባሩ በአፋጣኝ ካልተፈታ ጉዳዩን በሕግ አግባብ እንዲታይ እናደርጋለን" ያለ ሲሆን፤ ከቀናት በኋላም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ