ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 10 ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።

የዩኒቨርስቲዎች የቀጣይ የሪፎርም መዳረሻ ራስ ገዝ መሆን ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎቸ መሰራታቸውን ተናግረዋል።

"የትምህርት እና የምርምር ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር ራስ ገዝነት የተሻለ እድል ይፈጥራል" ሲሉም መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

ሚኒስትሩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

በዚህም "ጥራትን መሰረት አድርጎ የትምህርት ተቋማት ሀገር ተረካቢዎችና መሪዎችን በመቅረጽ ዩኒቨርሲቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰሩ ይገባል" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በቀጣይ ሊሰሩ የሚገቡት ላይ ማተኮር ይገባል" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዝግጅቶች የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 'ኢትዮጵያ የራሷ የጤና ባለሙያዎች ያስፈለጓታል' ተብሎ በ1942 በተነሳ ሃሳብ መነሻነት በተደረገ ጥረት፤ 1947 ዓ.ም የጤና ባለሙያ ማሰልጠኛ ሆኖ መመስቱ የዩኒቨርስቲው ታሪክ ያሳያል።

ዩኒቨርሲቲው አሁን ለደረሰበት ደረጃ በተለያየ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ሚና ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ተናግረዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ከ100 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁን ያስታወቀም ሲሆን፤ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ