ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ያለውን የቡና ምርት ሕገ-ወጥ ንግድ ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በክልሎች እና በከተሞች ያለውን የቡና ሕገወጥ ንግድ ለመቆጣጠር የኦንላይን አሰራርን በመዘርጋት ምዝገባዎች እንደተደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህ ሥራ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የቡና ንግድን ሲያካሂዱ በተገኙ አካላት ላይ በተወሰደ እርምጃ፤ 58 ሚሊየን ብር መገኘቱን የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"በተጨማሪም ይህን ሥራ ለማጠናከር ያግዛሉ የተባሉ አማራጮችን ሁሉ እየተጠቀምን ነው" ያሉ ሲሆን፤ የቅጣት ገንዘቡ ካምናው ተመሳሳይ ወቅት እንፃር መቀነሱን ተናግረዋል፡፡
"ለዚህም የሶፍት ዌሩ መልማት እና መተግበር፣ የጋራ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ መጠናከሩ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ መሆን ተጠቃሾቹ ናቸው" ብለዋል፡፡
የቡና ኮንትሮባንድ ንግድን ለማስቀረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እና ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታጣ ማድረግ ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከቡና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ 58 ሚሊየን ብር መገኘቱ ተገለጸ
