ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ በሚከሰቱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያት፤ አንዳንድ ብርቅዬ እንስሳት ላይ የመጥፋት አደጋ መጋረጡን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ አቦሸማኔ፣ አንበሳና ቀይ ቀበሮ የመጥፋ አደጋ ከተጋረጠባቸው የዱር እንስሳት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ለአሐዱ ገልጿል፡፡

አደጋው ከተጋረጠባቸው የዱር እንስሳት መካከል አቦሸማኔ በዋነኝነት የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፤ አቦሸማኔ በውስን ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ የሚገኝና ያለውም ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዱር እንስሳቱን ደህንነትን ለማስጠበቅ እና ዝርያቸው እየተመናመነ የሚገኘው እንስሳት እንዳይጠፋ ለማስቻልም፤ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ጣቢያም ቢሆን ከዚህ ቀደም የመመናመን ሁኔታ እየተስተዋለ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፤ ይህን ሁኔታ ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ለዱር እንስሳቱ መመናመን ሕገ-ወጥ ሰፈራ፣ ሕገ-ወጥ የደን መጨፍጨፍ፣ የእርሻ ሥራ እና የግጦሽ መበራከት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ለእንስሳቱ መመናመን አደጋ እየሆኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

አቶ ሰለሞን አክለውም፤ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክን እንደ ምሳሌ በማንሳት "ፓርኩ በሁለት ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፤ በፓርኩ ላይ የሚተዋለውን ሕገ-ወጥ ሰፈራ ለመቆጣጠር አስቻይ ሁኔታ እየተፈጠረ አይደለም" ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በፓርኩ ላይ እየተስተዋለ የሚገኘውን ሕገ-ወጥ ሰፈራ እና መሰል ችግሮች ለመፍታት ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር እየመከረ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በአንዳንድ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ሕገ-ወጥ አደን እንደሚስተዋል የገለጹ ሲሆን፤ ይህም እንስሳቱ ይበልጥ ለአደጋ ተጋላጭ እንዲሆኑና ቁጥራቸው እንዲመናመን ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም በተለያዩ ብሄራዊ ፓርኮች ላይ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር በባለስልጣኑ የተሰሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ በቀጣይም ከፓርክ አስተዳዳሪዎች፣ ከየአካባቢዎቹ የጸጥታ አካላት እና የኅብረተሰብ ክፍል ጋር የሚደረጉ መሰል እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ