ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ የተከሰተውን ርዕደ መሬት ተከትሎ፤ ከወረዳው ለተፈናቀሉ 7 ሺሕ 500 ሰዎች የፌዴራል አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ አመራሮች ጋር በመተባበር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል፡፡

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር አቶ አደም ባሂ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ለተፈናቃዮች የመጠለያና ምግብ ነክ ድጋፎች እንዲሁም ከክልሉ ጤና ቢሮና ከፌደራል ጤና ሚኒሲቴር ጋር በመቀናጀት ጊዜያዊ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም 'የተፈጠረው ችግር የሚቆይበት ጊዜ ስለማይታወቅ ተፈናቃይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቆም የለባቸውም' ተብሎ ስለታሰበ፤ ጊዜያዊ የመማሪያ ድንኳን በመትከል የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀመር የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እየተጓጓዙ መሆኑን ገልጸዋል።

አስተደዳሪው አክለውም፤ ከሰኞ በኋላ የመማር ማስተማር ሥራው እንደሚጀመር ለአሐዱ ተናግረዋል።

በተከሰተው አደጋ ከአጎራባች ክልል ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላገኙ የገለጹት አቶ አደም፤ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እያገኙ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አስተዳደሪው በወረዳው ከፍተኛ የመሬት መሰንጠቅ መኖሩን ገልጸው፤ ነዋሪዎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ጠቁመዋል።

በተያያዘም የሰመራ ዩንቨርስቲ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች ሂደቱን እየተከታተሉ ሙያዊ ድጋፍ እየሠጡ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ " አደጋ ይከሰትባቸዋል ከተባሉ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን የማውጣት ሥራ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡

በክልሉ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው ርዕደ መሬት ምክያት ከ58 ሺሕ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን በክልሉ ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታውቋል፡፡ በርዕደ መሬቱ ከ100 በላይ ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በርካታ እንሰሳቶች መሞታቸውም ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም በርዕደ መሬቱ ምክንያት፤ በአዋሽ ፋንታሌ፣ ዱላሳ እና ሓንሩካ ወረዳዎች በሚገኙ 37 ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 16 ትምህርተ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ፤ 21 ትምህርት ቤቶች ደግም ከፊል ጉዳት እንደረሰባቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡