ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 96 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ቀሪውን ሥራ ለማጠናቀቅ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን በዚህ ዓመት 110 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል፡፡

ይህንን የገንዘብ መጠን በተያዘው ዓመት በተለያዩ መንገዶች ለመሰብሰብ መታቀዱን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናግረዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንድሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች አሁንም ተሳትፎቸውን አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ መጀመሩ ተገልጿል።

ንቅናቄው የህዳሴ ግድብ ቦንድ ገዝተዉ የማያዉቁ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ በማድረግ እስከ 60 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ በማቀድ ተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ንቅናቄው ከዚህ ቀደም ቦንዱን ገዝተዉ የመመለሻ ጊዜዉ የደረሰ ቦንድ ያላቸዉ ደግሞ፤ በድጋሚ እንዲያድሱ በማድረግ 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብና በአጠቃላይ በዚህ ዓመት በድምሩ 1 መቶ 10 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረግን አላማው ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ ንቅንቄው ላይ የ32 ባንኮች፣ የ18 ኢንሹራንሽ ኩባንያዎችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቦርድ ሰብሳቢዎችና ፕሬዝደንቶች ተገኝተዋል፡፡

ይህ ድጋፍ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የንቅናቄው ተሳታፊዎች በጋራ እንደሚሰሩ ገለጸዋል፡፡