ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመዲናዋ በተያዘው የጥር ወር ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ የዲያስፖራ ንቅናቄ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታውቋል።

የዲያስፖራ ሳምንቱ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በሀገሪቱ በሚከናወን የልማት እንቅስቃሴ በሙሉ የባለቤትነት ስሜት መሳተፋ እንዲችል ለማድረግ የሚካሄድ መሆኑን፤ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ቅድስት ልዑልሰገድ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዲያስፖራው እርስ በርስ እንዲተዋወቅና ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ የዳበረ ሁኖ ሀገሩን የሚጠቅምበትን መንገድ ለማመቻቸት ያለመ መሆኑን አክለዋል።

የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቃልአብ ግርማ በበኩላቸው፤ "ከልማት፣ መዋዕለ ንዋይን ከማፍሰስና ከሥራ በተጨማሪ በሀገሩ ጉዳይ በቅርበት እንዲሳተፍ ከማስቻል አኳያ ዲያስፖራው ስለሀገሩ ያለው አመለካከትና እውቀት ይበልጥ እንዲጨምር ለማድረግ ነው" ብለዋል።

"የትኛውም ዲያስፖራ ለረዥም ዓመት በውጪ ሀገር ቢያሳልፍም ልቡ ሁሌም ሀገሩ ላይ በመሆኑ፤ ይሄ እንቅስቃሴ ዲያስፖራው የበለጠ ወደ ሀገሩ እንዲመጣና የተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፍ ያበረታታል ሲሉ" ገልጸዋል።

በተጨማሪም በወሩ ዲያስፕራው ማህበረሰብ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚጎበኝ ሲሆን፤ የፓናል ውይይት፣ የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት እና የእግር ጉዞ መርሃ ግብር እንደሚኖርም ተነግሯል፡፡

ይህ የመጀመሪያው የዳያስፖራ ወር እስከ ጥር 30 በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር የተገለጸም ሲሆን፤ ንቅናቄው በቶሮንቶ ካናዳም የሚቀጥል መሆኑ ተመላክቷል።