የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በምርጫ ቦርድ የተመዘገበ ተቋም ለማድረግ የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዉ በርካታ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዲሱ ሊቀመንበር የሆኑት የከፋ ሕዝቦች አረንጓዴ ፖርቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን አየለ፤ ዕዉቅና ያለዉ ተቋም እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ "ሕግ የለም ማለት አይቻልም" ያሉ ሲሆን፤ የተለያዩ ማዕቀፎችና መተዳደሪያ ደንቡ ለጋራ ምክር ቤቱ ቀርቦ መጽደቁን ገልጸዋል።
"ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ለጋራ ምክር ቤቱ እዉቅና ከመስጠት ዉጪ አማራጭ የለውም" ሲሉ የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ተናግረዋል።
አክለውም፤ አዲሱ አመራርም ሆነ ሥራ አስፈፃሚ ከቦርዱ ጋር በመሆን ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት በጋራ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምርጫ ቦርድ የቤት ኪራይ ተከራይቶ እንደሚያስተዳድረዉ ቢገልፅም "እዉቅና ነፍጎኛል" ሲል ግን ተደምጧል።
ይህንንም በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢያሳውቅም ምላሽ ማግኘት አለመቻሉንም መግለፁ ይታወሳል። ይህንን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ጥያቄ አንስተንላቸዉ የነበሩት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ዉብሸት አየለ፤ "ቦርዱ እዉቅና መስጠት ኃላፊነቱ አደለም" ብለዋል፡፡
"ምክር ቤቱ አሁን ባለበት መንገድ የሚቀጥል እንጂ፤ ፖርቲዎችን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠዉ ለምርጫ ቦርድ ብቻ ነው" ሲሉም ምክትል ሰብሳቢዉ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ "እውቅና የመስጠት ኃላፊነት የለኝም" እያለ ቢገልጽም፤ የጋራ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር "አማራጭ የለውም" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ምርጫ ቦርድ ለምክር ቤቱ ዕዉቅና ከመስጠት ውጪ አማራጭ የለዉም ሲል የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ
ሕዳር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምክር ቤቱ ዕዉቅና ከመስጠት ዉጪ አማራጭ የለዉም ሲል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገልጿል፡፡