መጋቢት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ሁሉን አካታች የሆነ ግዚያዊ አስተዳደር ማዋቀር አስፈላጊ ነው ሲሉ ለአሐዱ ሀሳባቸውን የሰጡ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ "ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ በህወሓት ቁጥጥር ውስጥ የሚሆን ጊዜያዊ አሰርተዳደር ለውጥ አያመጣም" ብለዋል፡፡
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያስተዳድራቸው የነበሩ ከከተማ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ታች ያሉ መዋቅሮች በህወሓት ቁጥጥር ሥር እየዋሉ አተዳዳዳሪዎች እየተቀየሩ ያለበት ሁኔታ መኖሩ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በዚህም ከሰሞኑ ለሦስት ወራት ያክል ያለ ከንቲባ የቆየችው መቀሌ ከተማን ጨምሮ አዲግራት እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የነበሩ አስተዳደሮች በህወሓት ቁጥጥር ሥር እየዋሉ መምጣታቸውን በመግለጽ፤ የግዚያዊ አስተዳደሩ ድርጊቱን "መፈንቅለ መንግሥት" ሲል ጠርቶታል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ አሐዱ ያነጋገራቸው የውድብ ናፅነት ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዶ/ር ደጀን መዝገቦ፤ "ከዚህ ወዲህ ሁሉን ያካተተ ግዜያዊ አስተዳደር መፍጠር ካልተቻለ ለውጥ ሊመጣ አይችልም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"ሁለት ዓመት ሙሉ ስንታገለው ነበር" ያሉት ሊቀመንበሩ፤ "ነገር ግን ምንም ለውጥ ማምጣት አልቻልንም" ብለዋል፡፡
"ለመሆኑ ጉዳዩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነና አሁን ያለው ችግር የሚባባስ ከሆነ ወዴት ሊያመራ ይችላል?" ሲል አሐዱ ላቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ደጀን ሲመልሱ፤ "ፖለቲካዊ መፍትሄ በአስቸኳይ ካልተሰጠው ትግራይ ላይ ብቻ የሚቆም አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በርካታ ጥያቄዎች እያሉት እና ጊዜያዊ አስተዳደሩም መፍታት ያለበት በርካታ ጥያቄዎች እያሉበት በዚህ ጉዳይ ላይ መጠመድ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
"የሚመለከታቸው አካላትም ቢሆን በትግራይ ጉዳይ ላይ ከህወሕት ጋር ብቻ መወያየታቸው ተገቢ አይደለም የትግራይ ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሌላው ሀሳባቸውን የሰጡት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "የፌደራል መንግሥት ቀድሞውንም ከሁሉም የተወጣጣ ጊዚያዊ አስተዳደር ማቋቋም ቢኖርበትም ይህንን ማድረግ አልቻልም" ብለዋል፡፡
"አሁንም ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት መመለስ አለብን" የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ "ይህ ባለመሆኑም ወደ ጦርነት ድባብ ልንመጣ ችለናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"ለመሆኑ የትግራይ ሕዝብ አሁን ካለበት ችግር አንፃር ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?" ሲል አሐዱ የጠየቃቸው ዶ/ር አረጋዊ፤ "ሕዝቡ ተቃውሞ ጀምሯል" ያሉ ሲሆን ተቋውሞ ባሰማ ቁጥር ግፉ እየበረታበት መሄዱም አንስተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ያለው ውጥረት ከፍ እያለ የመጣ ሲሆን፤ ከሰሞኑም በጊዚያዊ አሰተዳደሩ የታገዱት ወታደራዊ አመራሮች የጦር ትርዒት ሲያሳዩ መዋላቸው ብዙዎችን ሲያነጋር ቆይቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በትግራይ ክልል ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ሁሉን አካታች የሆነ ግዚያዊ አስተዳደር ማዋቀር አስፈላጊ ነው ተባለ
