መጋቢት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ባደረሰው መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት በትንሹ ከ340 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል።
በዚህም የእስራኤል የአየር ጥቃት በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት መሞታቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ክፍል ከ200 በላይ የአየር ጥቃቶች መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፤ በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈ ዜጎች ውስጥ ከ50 በላይ ሕጻናት እና 28 ሴቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።

ጥቃቶቹ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚኖሩባቸው ድንኳኖች እና ቤቶች ላይ ኢላማ ያደረጉ ሲሆን፤ ሴቶች፣ ሕጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎችን ማቁሰሉም ተነግሯል።
በተጨማሪም በጥቃቱ የጋዛ ሰርጥ አገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት የሃማስ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን ማሃሙድ አቡ ዋፋ መገደላቸው ተገልጿል።
የእስራዔል ጦር ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም የተጀመረው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ፤ በጋዛ "መጠነ ሰፊ" ጥቃት መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፤ የሃማስ የሆኑ "የሽብር ዒላማዎች" ላይ ማነጣጠሩንም አስታውቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ጥቃቱ እንዲፈጸም ማክሰኞ ጠዋት ማዘዛቸውን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

"ይህ የሆነው ሃማስ ታጋቾቻችንን ለመልቀቅ በተደጋጋሚ እምቢተኛ በመሆኑ እንዲሁም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት መልእክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከአደራዳሪዎች የቀረበለትን ምክረ ሀሳብ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው" ብሏል።
"እስራኤል ከአሁን በኋላ በሃማስ ላይ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ አጠናክራ ትቀጥላለች" ሲልም አስታውቋል።
የጥቃቱ እቅድ "በሳምንት መጨረሻ ላይ በእስራኤል መከላከያ ኃይል ቀርቦ በፖለቲካ አመራሩ ተቀባይነት አግኝቷል" ሲልም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
እስራኤል በቀጣይም ጥቃቱን በማጠናከር የምድር ውጊያ ልትጀመር እንደምትችልም ተመላክቷል፡፡
ሃማስ በበኩሉ "እስራኤል የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ለመቀልበስ ምንም የመከላከያ አቅም በሌላቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ 'አታላይ' ጥቃት አድርሳለች" ብሏል።
የእስራኤል የቦምብ ድብደባ በታጋቾች ላይ "የሞት ፍርድ" እንደማሳለፍ ይቆጠራል ሲልም ቡድኑ ጥቃቱን አውግዟል።

የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት አል ሪሽቅ፤ "የኔታንያሁ ዳግም ጦርነት የመጀመር ውሳኔ ታጋቾችን መስዋዕት የሚያደርጋቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ትናንት የተፈጸመው የእስራኤል የአየር ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነቱ መተግበር ከጀመረበት ያለፈው ጥር ወር አጋማሽ ወዲህ በአይነቱ ሰፊ መሆኑንም ነው የተገለጸው።
በርካታ ፍልስጤማውያን በረመዳን ጾም ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት በተደረገው በዚህ የአየር ድብደባ በጋዛ ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን የዓይን ምስክሮች ስለመናገራቸው ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
እንደ ዓይን ምስክሮቹ ገለፃ ከሆነ ከ20 በላይ እስራኤል ጦር አውሮፕላኖች የተመለከቱ ሲሆን፤ አውሮፕላኖቹ በጋዛ ከተማ፣ ራፋ፣ ካን ዩኒስ ዒላማዎቻቸው ላይ ቦንብ ማዝነብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ከእስራኤል ጋር ምክክር አድርጓል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ "ሃማስ፣ ሃውቲ፣ ኢራን እና ማንኛውም እስራኤል እና አሜሪካን ለማሸበር የሚሞክር ሃይል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋግመው ግልጽ አድርገዋል፤ የገሃነም በሮች በሰፊው ይከፈትላቸዋል" ሲሉ ገልጸዋል።

አሜሪካ እስራኤልና ሃማስ ከሁለት ሳምንት በፊት የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተኩስ አቁም ለ42 ቀናት እንዲያራዝሙ ምክረሃሳብ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡
በዚህም የመጀመሪያውን ምዕራፍ እስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ድረስ እንዲራዘም፣ እንዲሁም ሃማስ ያየዛቸውን ታጋቾች እንዲለቅ፣ እስራኤል ያሰረቻቸውን ፍልስጤማውያን እንድትፈታ ሀሳብ አቅርባ ነበር።
ነገር ግን ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ እስራኤል እና ሃማስ በሦስተኛ ወገን በኩል ባደረጉት ድርድር ላይ የአሜሪካው ተወካይ ዊትኮፍ ባስቀመጡት የስምምነት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አለመግባባታቸውን ተናግረዋል።
እአአ ጥቅምት 7 ቀን 2023 በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በተጀመረው ጦርነት ምክንያት እስካሁን ድረስ ከ48 ሺሕ 520 የሚበልጡ ሰዎችን መሞታቸውን እና አብዛኞቹ ሲቪሎች እንደሆኑ በሃማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
1 ነጠብ 2 ሚሊዮን የሚሆነው በጋዛ ሰርጥ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል አብዛኛው በተደጋጋሚ መፈናቀሉም ተነግሯል።
በተጨማሪም በግምት 70 በመቶ የሚሆኑ ሕንፃዎች የጤና አጠባበቅ፣ የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶች የወደሙ ሲሆን፤ በጋዛ የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድሃኒት እና የመጠለያ እጥረት መፈጠሩም ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ