ጥር 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በተያዘው የ2017 ግማሽ ዓመት በሕገ-ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ ከ35 ሺሕ 900 ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

በክልሉ በተያዘው ግማሽ ዓመት ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቀረት ሲሰራ የነበረ ሲሆን፤ በዚህም በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር መሰረት ነዳጁ ሊያዝ መቻሉን፤ በቢሮው የፕላን ልማትና እቅድ ዳይሬክተር አቶ ሐጎስ ግርማይ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም እንደ አጠቃላይ በክልሉ እየገባ ያለው ነዳጅ አነስተኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በ6 ወራት ውስጥ ከታቀደው 67 በመቶው ብቻ ወደ ክልሉ የገባ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህም ካለው ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቤንዚል ከጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ክልሉ እየደረሰ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

"ይህንን ችግር መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እየተሰራ ቢሆንም፤ አሁንም በቂ የሆነ አቅርቦት የለም" ብለዋል፡፡

ባለው ነዳጅ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆንም ነዳጅ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳይዘዋወር ወይንም እንዳይሸጥ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

እንደ አጠቃላይ ያሉ ግብአቶችን በመጠቀም ሕገ-ወጥ ግብይትን ለመቀነስ በቀጣይ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሰሩም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ