ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት በመጀመሪያ 6 ወራት ላይ 64 ሺሕ 256 ለሚደርሱ ታካሚዎች በተመላላሽ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገልጿል።

ሆስፒታሉ ለአሓዱ በላከው መግለጫ በየዕለቱ ሕክምና ሳያገኙ የተመለሱ ሕሙማን በስድስት ወራት ውስጥ አለመኖራቸውን ጠቁሟል።

በ6 ወራትም 257 የሚሆኑት የሕጻናት የአእምሮ ሕክምና ያገኙ ሲሆን፤ በሱስ ሕክምና ደግሞ 410 ለሚደርሱ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል ብሏል፡፡
በተጨማሪም 921 ታካሚዎች በተኝቶ የአእምሮ ሕክምና አገልግሎቱን መስጠት መቻሉ ተገልጿል፡፡

"የተኝቶና ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ከተሰጡት ውስጥ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት 36 ሺሕ 300 የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው" ሲል ገልጿል፡፡

በተመላላሽና በተኝቶ ሕክምና በመጀመሪያ 6 ወራት ውስጥ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ተመርማሪ ለሆኑ 413 ሰዎች አገልግሎት ማግኘታቸውም ተመላክቷል።

በዚህም በሆስፒታሉ ጤና ጣቢያ ጥምረት ለጥራት፤ በሥነ-አእምሮ ሕክምናና የጥራት ማሻሻያ ፕሮጀክት ፅንሰ ሃሳብና ትግበራ በተመለከተ፤ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሥር ለሚገኙ 17 ጤና ጣቢያዎች ስልጠናና ተከታታይ ድጋፍ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የአዕምሮ ጤና አገልግሎት በጤና ተቋም ደረጃ መሰጠት የጀመረው በ1928 ዓ.ም በጣሊያን ወረራ ወቅት ነው፡፡

በወቅቱም ለሀገሪቱ ዜጎች አጠቃላይ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ታቅዶ በጊዜው ከዋናው ከተማ ወጣ ብሎ በከተማው ጫፍ ጥቅጥቅ ባለው ገጠራማ ቦታ በተሰራውና በወቅቱ መጠሪያው ተክለሀይማኖት ሀኪም ቤት፤ በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሆነው ተቋም ውስጥ አገልግሎቱን መጀመሩ ይታወቃል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ