ጥር 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘ 923 አቤቱታዎች መቅረባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ በስድስት ወራት ውስጥ በ1 ሺሕ 800 ተቋማት ላይ በድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘ እርምጃ ስለመወሰዱም ተናግሯል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለባስልጣኑ መስሪያ ቤት ከቀረቡ ከ923 አቤቱታዎች መካከል አብዛኞቹ ከጭፈራ ቤት ጋር በተያያዘ የሚቀርብ የድምጽ ብክለት ስለመሆኑ የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ በስድስት ወራት ውስጥ በተከናወኑ ሥራዎች ከዚህ ቀደም ከሚተስተወሉት አንጻር ለውጦች የታዩባቸው ስለመሆናቸውም አስረድተዋል፡፡

የአካባቢ ብክለት እንዳይከሰት ከ7 ሺሕ 300 በላይ አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራ ለማከናወን እቅድ ተይዞ እንደነበር የገለጹም ሲሆን፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ8 ሺሕ 772 ተቋማት ላይ የክትትል ሥራ ስለመከናወኑ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ እንደሚሰድ ገልጸው፤ በ50 የጭፈራ ቤቶች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የግንዛቤ እጥረት እንዳይፈጠር እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ በሚስተዋሉ ለውጦች ሳይገደብ የቁጥጥር ሥራ ምሽት ላይ የሚከናወን ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሚከናወን ድንገተኛ የድምጽ ብክለት ቀጥጥር ላይ ተደጋጋሚ የሆነ ጥፋት በሚያደርሱ ተቋማት ላይ የንግድ ፍቃድን እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር ስለመኖሩም ለአሐዱ አስታውቀዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ