ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አውጥቶት የነበረውና 'የመሸጋገሪያ ደንብ' ብሎ የጠራውን ድንብ ቁጥር 4 ለቀጣይ አንድ ዓመት እንዲራዘም መውሰኑ የቀድሞ የፖሊስ አባላት ደመወዝ እንዳይከፈላቸው ማድረጉን የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ የትግራይ ቅርጫፍ አስታውቋል፡፡
ቅርጫፍ ጽ/ቤቱ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ በማጣቱ ወደ ክስ ሊያመራ መሆኑን ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህንን በሚመለከት አሐዱ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ትግራይ ቅርጫፍን የጠየቀ ሲሆን፤ የቅጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ፀሐዬ እምባዬ "አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም፤ ውጤት ግን ማግኘት አልተቻለም" ብለዋል፡፡
ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ረዳት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚገለጹት ኃላፊው፤ "ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንቱ ረዳት ጉዳዩን መፍታት አለቻሉም" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ቀጥታ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸውንና በዚህ ውይይት መፍትሄ ይመጣል ብለው እንደሚጠብቁ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
"ለመሆኑ በጊዚያዊ አስተዳደሩ ያወጣውን ደንብ ቁጥር 4 ለቀጣይ ዓመታት መራዘሙ በቀድሞ የፖለሲ አባላት ላይ የሚፈጥረው ችግር ምን ይሆን?" ስንል የእምባ ጠባቂ ኃላፊውን ጠይቀናል፡፡ በምላሻቸዉም በመጀመሪያም ደንቡ በራሱ ችግር ያለበትና መሠረታዊ ዜጎችን መብት የሚገድብ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የደንቡ መራዘም ቀድሞ የፖሊስ አባላት ደመወዝ እና ወደ ሥራ የመመለስ ጥያቄን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ ያሉ በርካታ ችግሮችን ያባባሰ መሆኑን የቅርጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
"የደንቡ ጊዜ መጠናቀቅን ተከትሎ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ቀድሞ ፖሊስ አባላት ደመወዝ እና ወደ ሥራ የመመለስ ጥያቄን እናነሳለን" የሚሉት አቶ ፀሐዬ፤ "በአሁን ሰዓት ግን ስለደመወዝ መጠየቅ አንችልም" ብለዋል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ የፖሊስ አባላትን 'በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ወደ ጦርነት አልሄዳችሁም' በሚል፤ ከሥራ ስለማሰናበቱና ደመወዝ ስለማገዱ ቅርጫፍ ጽ/ቤቱ ከዚህ በፊት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኃላ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ወደ ሥራ የተመለሰ ቢሆንም፤ የፖሊስ አባላቶቹ ግን ደመወዝ አለማግኘታቸው እንዲሁም ወደ ሌላ ሥራ እንዳይገቡም ክሊራስ ወይም መሸኛ ጭምር እንዳልተሰጣቸው ተገልጿል፡፡
አጠቃላይ ከሥራ ውጭ የሆኑት የፖሊስ አባላት ብዛትም 3 ሺሕ 200 እንደሚሆኑም ለእንባ ጠባቂ ተቋሙ አስታውቀዋል፡፡