ታሕሳስ 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ልማት ኢንተርፕራይዝ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 4 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ለአምራች ኢንተርፕራይዙ መስጠቱን የገለጸ ሲሆን፤ ብድሩም ለማሽነሪ እና የሥራ ማስኬጃ የሚውል መሆኑን አስታውቋል።
እንዲሁም አምራቾች የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር የገበያ ዕድል የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዱልፈታ የሱፍ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ይህም ብድር የተለያዩ ግብዓቶችን ለኢንዱስትሪ የሚያቀርቡ አካላት ለኢንተርፕራይዞች በተሟላ መልኩ እንዲያቀርቡ የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል።
እንዲሁም "በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት ዘርፉን በተሟላ እውቀትና ብቃት መደገፍ እንዲችሉ አቅም የመገንባት ሥራ ይሰራል" ብለዋል።
አምራች ኢንተርፕራይዞች በተደጋጋሚ የጥራት ችግር እንደሚነሳባቸው የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ "ይሄ አሁን ጥራት ያላቸው ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ የሚልኩ የውጭ ሀገራት በአንድ ጊዜ ብቁ የሆኑ አይደሉም" ብለዋል።
በዚህም ለአምራች ኢንተርፕራይዙ ከሸማቹ ጋር በመነጋገር እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ጥራት ያላቸው ምርቶችን ማምረት እንደሚቻል ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የንግድ ልማት አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ በአማካሪ ድርጅት አማካኝነት ጥናት መደረጉንና ችግሮችና ክፍተቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።
"ጥናቱን መሰረት በማድረግም እንደመነሻ ለተመረጡ 400 ኢንተርፕራይዞች የንግድ ልማት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል" ብለዋል።
አምራች ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል የዘርፉ ልማት ፍኖተ ካርታ፣ የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ስትራቴጂ፣ የተኪ ምርት፣ የቆዳ ልማት፣ የትስስር፣ እና ሌሎች ስትራቴጂዎች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ሰነዶች እንዲዘጋጁ መደረጉንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው ምርቶቻቸውን በጥራት እንዲያመርቱና የተወዳዳሪነት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ መሰራቱ ተገልጿል።
በዚህም የዘርፉ ልማት የብዙ ተቋማትን ተሳትፎና ድጋፍ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለፋት ዓመታት ቅንጅታዊ ትግበራ ላይ ክፍተቶች የነበሩበት እንደሆነም ተነስቷል።
በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተዘጋጀና የአምራች ኢንተርፕራይዞችን የግብይት አቅም ለማሳደግና ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠር ያለመ "የእኛ ምርት ለእኛ" የተሰኘ ባዛር፤ ከታሕሳስ 18 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ መከናወኑ ይታወቃል።
አምራች ኢንተርፕራይዞች ባለፈው ዓመት ብቻ 4 ቢሊየን ብር ብድር እንዲያገኙ መደረጉ ተገለጸ
ለ400 ኢንተርፕራይዞች የንግድ ልማት አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተነግሯል