መጋቢት 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ብቻ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በክልሉ ከ3 ሺሕ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራው ውጭ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በንቅናቄ መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ "ትምህርት ቤቶች ለልጆቻችን አመች፣ ዕውቀት መቀበል የሚችሉ ደስተኛ ልጆች ለማፍራት የሚያስችሉ እንዲሆኑ በመላው ሀገሪቱ እየሠራን ነው" ብለዋል።
"በተለያዩ ክልሎች የተነሱ ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ እያደረግን ያለነውን የለውጥ ሂደት ክፉኛ እየተፈታተኑት ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "ግጭቶቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ያሉትንም ሕጻናት እና ወጣቶች በትምህርት ሊያገኙት የሚችለውን የወደፊት ዕድል ክፉኛ ሲያጨናግፉት እናያለን" ብለዋል።
"ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት እና የግጭቱ ጦስ በነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት እና ወጣቶች ላይ ያመጣውን እና እያስከተለው ያለውን የሥነ ልቦና ጠባሳ ሳይ ከፍተኛ ቁጭት እና ሀዘን ይሰማኛል" ሲሉም ተናግረዋል።
በንቅናቄው በመላ ሀገሪቱ ኅብረተሰቡ ልጆቹን ለማስተማር ያለውን ፍላጎት እና ከፍተኛ ትጋት ማየታቸውንም አንሰተዋል።
ግጭቶች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች የትምህርት ሥርዓቱ ክፉኛ ከሚጠቁ ዘርፎች አንዱ መሆኑንም አንስተዋል። "ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ሕጻናት በብዙ መልኩ ከማንም በላይ ተጎጂ ናቸው" ሲሉም ገልጸዋል።
"ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ "ሕጻናት ወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን የሚገነቡበት፣ ችሎታቸውን የሚከፍቱበት ቁልፍ መሳሪያ እና ድልድይ ነው" ብለዋል። "ነገር ግን በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚካሄድ ግጭት እና ጦርነት ይህን መብት እየጣሰ ነው" ብለዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንም አንሰተዋል።
"የትጥቅ ግጭት የሚያስከትለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፣ ትምህርት ቤቶች ይወድማሉ፤ መምህራን ይፈናቀላሉ፣ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ይለቃሉ፣ በብዙ ዘመን እና ድካም የተገነባውን የኅብረተሰቡን መዋቅር የሚያፈርስ እና የሕጻናት እና ወጣቶችን ብሩህ የወደፊት ተስፋ የሚሸረሽር ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግጭት ብሎም ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተባቸው ከልሎች በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ሲሉም ተናግረዋል።
"በዚህ ዓመት እንደ ሀገር ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባቸው ውስጥ፤ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ" ብለዋል።
በአማራ ክልል ብቻ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ያሉም ሲሆን፤ ከ3 ሺሕ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራው ውጭ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ "የዚህን ክፉ ተግባር ውጤት ምንነት ከዛሬም በላይ ገና ወደፊት ይገለጣል" ብለዋል።
የግጭቱ ሰለባ የሆኑ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦ ጫና እየደረሰባቸው እና የተማሪዎች የወደፊት የሕይወት ዕድል እየተሰናከለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ከልል ልጆች እና ወጣቶች በሌሎች ክልሎች ካሉ እኩዮቻቸውም ይሁን ሰላም ባለባቸው አካባቢ ካሉ ልጆች አንጻር ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው መገንዘብ ይቻላል ነው ያሉት።
"ትምህርት የረጅም ጊዜ ሥራ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "ትምህርት በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት ሲቋረጥ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና ጫና እጅግ ከባድ ነው" ብለዋል።
እነዚህ ልጆች ወደ ትምህርታቸው ተመልሰው ቢገቡም እንኳን የደረሰባቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ትምህርት የመቀበል አቅማቸውን እንደሚጎዳው ነው የተናገሩት። በተጨማሪም በግጭት ጊዜ ያለፈውን ትምህርት ለማካካስ አስቸጋሪ ይኾናል ብለዋል።
"እንደምንም አካክሰው እንኳን ትምህርታችውን ቢቀጥሉ በዕድሜ ከነሱ ካነሱ እና ከታናናሾቻቸው ጋር መማራቸው ጫናውን የጎላ ያደርገዋል" ነው ያሉት።
አክለውም "ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል በጦርነት የፈረሱ 45 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብተን አስረከበናል" ብለዋል።
በዚህ ዓመት ሁለተኛ ደረጃ ትምህትት ቤቶች ላይ በማተኮር 17 ትምህርት ቤቶችን በአማራ ከልል ለመገንባት ተዘጋጅተናል ሲሉም ተናግረዋል።
"የሁሉንም ትምህርት ቤቶች ግንባታ ክረምት ከመግባቱ በፊት እናስጀምራለን" ያሉት ሚኒስትሩ፤ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቀቁም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ሚኒስቴሩ አክለውም የአማራ ክልል ከግጭት ወጥቶ፤ ከትምህርት ገበታ የራቁትን ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤቶች ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ትምህርት ሚኒስቴር በተቻለው አቅም ሁሉ እንደሚተባበር አስታውቀዋል።
"ትምህርት ለትውልድ" የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ የተሳካ እንዲሆን በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች፣ የቀድሞ ተማሪዎች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች በትውልድ ቦታቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ