ጥር 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ምክንያት ተጠያቂ ባላቸው 29 የተቋሙ ሠራተኞች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታውቋል።
ከነዚህም ውስጥ 6 ያህሉ ከሥራ የተሰናበቱ ሲሆን፤ 23ቱ የደሞዝ ቅጣት የተጣለባቸው መሆኑ ታውቋል።
ብልሹ አሰራርን ለመግታት የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ሁሉም አካል ግንዛቤ እንዲኖረው መደረጉን የገለጹት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል አድማሱ ተክሌ፤ በዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ ለአሐዱ አስታውቀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ 67 ሠራተኞች ላይ እርምጃ የወሰደበት ጊዜ እንደነበረ ተጠቅሷል። በዚህም መሰረት የዘንድሮው ዓመት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂነት የቀነሰበት መሆኑ ተመላክቷል።
ለተጠያቂነት መቀነስም በብልሹ አሰራር ዙሪያ ለኅብረተሰቡና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከ11 ክፍለ ከተማና ከ119 ወረዳዎች ለተመለመሉ ተባባሪ አካላት ግንዛቤ በመፈጠሩና ጥቆማ በመስጠት ቀድሞ መከላከል በመቻሉ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም በተቋሙ ውስጥ አንዱ ሌላኛውን የማጋለጥ ተግባር መከናወኑ አወንታዊ አሰተዋፅኦ ማድረጉ ተነግሯል፡፡
ለአብነትም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ምደባ ለማግኘት ጥረት ያደረጉትን ማጋለጥ መቻላቸው እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀስ መሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ