ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ 59 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዘራ ታደሰ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ድጋፉ የተደረገው ከዓመት በፊት በኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበር በተገኘ የገንዘብ ድጎማ በተሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡
በዚህም "በሰሜን ወሎ ጃራ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ 1 ሺሕ 560 ዜጎች፣ በደቡብ ወሎ ደግሞ ተንታ እና ደሴ ዙሪያ አካባቢዎች በጦርነቱ ለተጎዱ ማህበረሰቦች በአጠቃላይ 59 ሺሕ ለሚሆኑ ተጎጂዎች ደርሷል" ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ በመፈጠሩ በተለይም ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተጋላጭ በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራበት እንደቆየ ተናግረዋል።
በመሆኑም ለአንድ አባወራ በሦስት ዙር 21 ሺሕ ብር የሚሆን በአጠቃላይም 2 ሺሕ 560 ለሚሆኑ እማወራዎችና አባወራዎች 56 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስቸኳይ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ወጪ መደረጉን እንዲሁም የእርባታ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
"120 ለሚሆኑ ሴቶች ደግሞ ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን 5 ሚሊዮን 200 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ራሳቸውን እንዲቀይሩ ተሰርቷል" ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ የፈረሱ 7 የውሀ ተቋማትን ማደስና ማስረከብ መቻሉን እንዲሁም፤ 10 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች አስፈላጊ ወጪዎችን በመሸፈን ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ አክለው ገልጸዋል።
በእርዳታ አሰጣጡ ሂደት ላይ የሚገጥሙ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት የፕሮጀክት አስተባባሪው፤ ሆኖም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያለው አመለካከት ጥሩ በመሆኑ ሥራውን በሚገባ ለማከናወን እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም ከኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበር በተገኘ ድጋፍ ሌሎች ሦስት ወረዳዎችን ጨምሮ ለ18 ወራት የሚቆይ ተመሳሳይ አገልግሎት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
"በዚህ ፕሮጀክት በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተከሰተው ረሀብና ድርቅስ ምን አይነት ሥራዎች ተከናወኑ?" ብሎ አሐዱ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ ከፕሮጀክቱ አጣዳፊ ጉዳይ ሲያጋጥም አስቀድሞ በተዘጋጀው በጀት መሰረት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለማቅረብ ግዢው በሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ