ጥር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዋሽንግተን ዲሲ የመንገደኞች አውሮፕላን ከወታደራዊ ሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ የ67 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ክስተት በሠራተኞች እጥረት ምክንያት ተከስቷል በሚለው ጉዳይ ላይ ባለስልጣናት ምርመራ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡
አደጋ የደረሰበት የመንገደኞች አውሮፕላን ጥቁር ሣጥኖች የተገኙም ሲሆን፤ በሠራተኞች ቁጥር እና አውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ በተወሰኑት ውሳኔዎች ዙሪያ ጥያቄዎች እየተነሱ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በአካባቢው ለሚበሩ ሄሊኮፕተሮች እና አውሮፕላኖች በተለምዶ ሁለት ሰዎች የአየር ትራፊክ ቁጥጥሩን የሚያከናውኑ ቢሆንም፤ ግን በአደጋው ወቅት አንድ ሰው ብቻ እንደነበር ሲቢኤስ ኒውስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ (ኤንቲኤስቢ) የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በ30 ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል።
የበረራ ዳታ መቅጃ እና ኮክፒት ድምጽ መቅጃ የሆኑት ጥቁር ብላክ ሣጥኖች በበረራ ላይ ምን ችግር እንዳለ ፍንጭ ለመስጠት ይረዳሉም ተብሏል።
ሣጥኖቹ ወደ ኤንቲኤስቢ ቤተሙከራ እንደተወሰዱ እና ምርመራ እንደሚከናወን ሲቢኤስን ጠቅሶ ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
በኒውዮርክ ታይምስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገበው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሰው ሃይል ቁጥር ጉዳይ "ያልተለመደ አይደለም" በሚል በፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ተገልጿል።
በሬጋን ዋሽንግተን ብሔራዊ አውሮፕላን ማረፊያ አንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሄሊኮፕተሮችን እና አውሮፕላኖችን የሚቆጣጠርበት አሠራር የተለመደ እና መመሪያዎችን ያልጣሰ ነው ተብሏል።
ውሃ ጠላቂዎች ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለው በፖቶማክ ወንዝ የተጎጂዎችን አስከሬን በመፈለግ ያሳለፉ ሲሆን፤ የማፈላለግ ሥራው ሐሙስ ማምሻውን በአደገኛ ሁኔታ ምክንያት ተቋርጧል።
እስካሁን ከአውሮፕላኑ 27 እና ከሄሊኮፕተሩ ደግሞ አንድ አስከሬን ማግኘት መቻሉም ነው የተገለጸው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የ67 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የዋሽንግተን ዲሲው የአውሮፕላን አደጋ በሠራተኞች እጥረት ምክንያት ተከስቷል በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ ተከፈተ
የበረራ መረጃ መቅጃ እና ኮክፒት ድምጽ መቅጃ የሆኑት ጥቁር ብላክ ሣጥኖች ተገኝተዋል ተብሏል