ጥር 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አስገዳጅ ደረጃዎችን ሳያሟሉ ጥራታቸውን ያልጠበቁ የሕፃናት ምግብ እና መጠጥ ምርቶችን በገበያ ላይ ያሰራጩ ከ30 በላይ ፋብሪካዎች ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ ተቋማቱ ላይ እርምጃ የወሰደው ባካሄደው ድንገተኛ አሰሳ አስገዳጅ ደረጃዎችን ጨምሮ ሌሎች የምርት ጥራትን የሚቀንሱ ተግባራት ሲያከናውኑ በማግኘቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፤ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ለገበያ ከቀረቡ በኋላ ከማስወገድና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከማገድ በተጨማሪ የቅድመ ምርት እና የድህረ ምርት ቁጥጥር እንደሚያደርግ፤ የባለሥልጣኑ የምግብ ኢንስፔክሽን ሕግ ማስፈፀም ሥራ አስፈፃሚ ሙላቱ ተስፋዬ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ከምርት ግብአት እስከ መጨረሻው ውጤት ድረስ በሚካሄደው የቁጥጥር ሥራ ለገበያ በሚቀርቡ ማናቸውም ምግብ ነክ ምርቶች የጤና ጉዳት አለማስከተላቸው እንደሚረጋገጥም አንስተዋል፡፡

ጥራታቸውን ሳይጠብቁ በሕገ-ወጥ መንገድ ተመርተው የተገኙት የሕጻናት ምግቦች ሊያዙ የቻሉትም በተገለጸው የክትትል ሂደት መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡም በሕገ-ወጥ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለሕግ አሳልፎ በመስጠት የመፍትሔው አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሥራ አስፈፃሚው አያይዘውም የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጠንካራ ተቆጣጣሪ ተቋም በመሆን ከሚያከናውናቸው ተግባራት የሚገኙ ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የጥራት አስተዳደር ስርዓት ዘርግቶ እየሰራ እንደሚገኝ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ