የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚፈፀሙ እገታዎች እና ግድያዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ባለመወሰዱ አዳዲስ መስመሮችም የእገታ ተግባራት እየተፈፀመባቸው ነው ሲል ጣና የአሽከርካሪዎች ማህበር ለአሐዱ ገልጿል፡፡

በቅርቡም በጭልጋ እንዲሁም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች መተሃራን ጨምሮ የሞቱ አሽከርካሪዎች ቁጥር በርካታ መሆኑን የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ሰጡ ብርሃን ተናግረዋል፡፡

ከአዋሽ መተሃራ የተሸከርካሪዎች መቃጠልና የሚፈፀሙ እገታዎች ተበራክተው መቀጠላቸውን የሚናገሩት የማህበሩ ዋና ፀሐፊ፤ "በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ከዚህ ቀደም በስፋት እገታ ያልነበረባቸው እንደ ደባርቅ እና ከጎንደር መተማ ያሉ መንገዶች ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም የመተማውን መንገድ በመስጋት አሽከርካሪዎች በሌላ ተለዋጭ መንገዶች እየሄዱ ለተጨማሪ ወጪ እና እንግልት እየተዳረጉ እንደሚገኙ አቶ ሰጡ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

"ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ቦታዎች ላይ እገታ፣ ግድያና ዘረፋ መበራከቱ ከዚህ ቀደም የተወሰደ እርምጃ ባለመኖሩ ነው" ሲሉም ወቅሰዋል፡፡

አክለውም "አንድ አጋች ከአሽከርካሪ ላይ እስከ 500 ሺሕ እና 1ሚሊዮን ብር ድረስ የሚቀበል ከሆነና የሚጠይቀው ከሌለ መበራከቱ የሚቀንስበት ሁኔታ የለም" ብለዋል፡፡

ማህበሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ከአሽከርካሪዎች መታገትና ጉዳት መድረስ በዘለለ የሞቱ አሽከርካሪዎች ከ250 በላዩ መደረሱን የማህበሩ ዋና ጸሀፊ ገልጸዋል፡፡

ይህ ሁኔታ በተለይም ከወደብ ጋር የሚገናኙ አካባቢዎች ላይ እየፈጠረ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ተብሏል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር በዚህ ጉዳይ ላይ እየወሰደ ያለውን እምርጃ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጠን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም ፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ