የካቲት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ ያካሄደበትን የምርጫ ምዝገባና ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ምርጫ ቦርድ ጥር 8 እና 9 2017 ዓ.ም በአዋጅ 1162/2011 ረቂቅ ላይ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት ያረገበት ቢሆንም፤ 'ውይይቱ በቂ አይደለም' በሚል ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ባቀረቡት መሰረት ቦርዱ ጥያቄያቸውን በፅሁፍ እንዲያስገቡ አሳውቋል፡፡

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) 'መስተካል አለባቸው' ያላቸውን ቅሬታዎች በሚመለከት 19 ገፅ የያዘ ሰነድ ለቦርዱ ማስገባቱን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅን ማሻሻሉ በጎ ጎን ቢኖረውም አሳሪ የሆኑ አንቀጾች የተካተቱበት መሆኑን የሚናገሩት፤ የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሐይማኖት ናቸው፡፡

" 'የመንግሥት ሠራተኛ ምርጫ ለመወዳደር ያለ ደመወዝ የሦስት ወር ፍቃድ መውጣት አለበት' የሚለው ረቂቅ አዋጅ ተገቢነት የሌለው ነው" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ድኤታዎችን እና የፌደራልና የክልል ባለስልጣናትን አለማካተቱ በዋናነት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ተጽኖ የሚያሳድር በመሆኑ አዋጁን ቦርዱ በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አብሃም ጌጡ በኩላቸው፤ "የመንግሥት ሠራተኛው ከደመወዝ ውጪ ፍቃድ ይውጣ የሚለው የመንግሥት ተቀጣሪውን ከፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲገለል የሚያድረግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው 15 የሚሆኑ ነጥቦችን እንዲሻሻሉ ለቦርዱ ማስገባቱን አንስተው፤ የመንግሥት ሠራተኛው ላይ የተደረገው ጫና ሕገ-መንግሥታዊ ባለመሆኑ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነባሩን አዋጅ ለማሻሻል 'ይመለከታቸዋል' ካላቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ሲሆን፤ የቀረበለትን ማሻሸያዎች ተቀብሎ በአዋጁ ላይ እንደሚያካተው ተስፋ እንዳላቸው ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ