ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 አርሴማ ፀበል አከባቢ ከነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5፡00 እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡30 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፤ ፀሃዬ ቦጋለ በየነ የተባለ ተከሳሽ ባለቤቱ የነበረችውን ሟች በአሰቃቂ ሁኔታ ከኋላዋ በመምታት እራሷን እንድትስት ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በማስከተልም እዛው ትቷት ከቤት ወጥቶ በመሄድና ከተወሰነ ሰዓታት በኋላ ተመልሶ በመምጣት ሟች እራሷን ስታ ከወደቀችበት፤ ሰውነቷን በአሰቃቂ ሁኔታ በመቆራረጥ ሽንት ቤት ውስጥ መጨመሩ ተነግሯል፡፡

ግለሰቡ የሟችን ቀሪ አስከሬን እዛው መታጠቢያ ቤት ውስጥ በማስቀመጥ እስከ 30/12/2014 ዓ.ም ድረስ ምንም እንዳልተፈጠረ እቤት ውስጥ እያደረ ቆይቷልም ተብሏል፡፡

በኋላም ከ1/13/2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 16/1/2015 ዓ.ም ድረስ ቤቱን ዘግቶ በመሰወሩ ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ማጣራት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡም በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕጻናት ላይ ሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ539/1/ሀ/ መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሒደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም የመከላከያ ማስረጃ አቅርቦ የቀረበበትን ክስ ሊከላከል አለመቻሉ ተነግሯል፡፡

ፍርድ ቤቱም በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ተመላክቷል፡፡

ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ይግባኝ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የወሰነውን የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ውሳኔ በመሻር ተከሳሹ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ