ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት እስካሁን ባለው ጊዜ 48 አዳዲስ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መለየታቸውን የከተማዋ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በከተማዋ 'ለጎርፍ እና ለሌሎችም አደጋዎች ተጋላጭ ናቸው' ተብለው የተለዩ ቦታዎችን ለሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የሚሰጠው ኮሚሽኑ፤ በየጊዜው አደጋ ሊያጋጥምባቸው ይችላሉ የተባሉ ቦታዎችን እንደሚለይ ይታወቃል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አሐዱ ያነጋገራቸው በኮሚሽን መስሪያ ቤቱ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎች ልየታ ባለሙያ አቶ ያሬድ ዳምጠው፤ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ባለው ጊዜ 48 የሚሆኑ አዳዲስ የተለዩ ቦታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

"በተጨማሪም እስከ ክረምት ሌሎች ቦታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል" ብለዋል፡፡

"ከዚህ በፊት 'ለአደጋ ታጋላጭ ናቸው' ተብለው ከተለዩት 505 ቦታዎች 117ቱን ማቃለል ተችሏል" ያሉም ሲሆን፤ በአጠቃላይ ካሉ ተጋላጭ ቦታዎች ውስጥ 227 ቦታዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም ከእነዚህ ቦታዎች ውስጥ 142 ቦታዎች ላይ ሥራዎች ተሰርተው የማይፈቱ ከሆነ ችግር የሚያስከትሉ እና በከፍተኛ ተጋላጭነት ደረጃ ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን አቶ ያሬድ ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሉ ባለድርሻ ናቸው የሚባሉ ተቋማት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ተከፋፍለው የሚሰጧቸው ቢሆንም ያለው ምላሽ ዝቅተኛ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ካሉት ለአደጋ ተጋላጭ ቦታዎች እንጻር የተሰጡ ምላሾች ዝቅተኛ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

አሐዱም "አስፈፃሚ የማይሆኑ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የወጣውን መመሪያ ተከትሎ፤ የተሰሩ ሥራዎች አሉ ወይ? ተጠያቂነቱስ" ሲል አቶ ያሬድን ጠይቋል፡፡

ባለሙያው በሰጡት ምላሽም ተቋማቱ ስለችግሮቹ ግንዛቤው አላቸው ነገር ግን ያለው የኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እየፈተናቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎች ልየታ ባለሙያው አቶ ያሬድ አክለውም፤ የጎርፍ እና ሌሎችም አደጋዎች ሊከሰቱ የሚችሉባቸው ቦታዎች ካሉ ማህበረሰቡ እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ