ታሕሳስ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ግዜ በድሬደዋ ደግሞ ለመጀመሪያ ግዜ የሚደረገው ‘የአእላፋት ዝማሬ’ ወይም "The Melody of Myriads" የተሰኘው የዝማሬ መረሀግብር በገና ዋዜማ ታሕሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚካሔደውን ዓመታዊ የዝማሬ ሁነት የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ የመጀመሪያውን የአእላፋት ዝማሬ በ2016 ዓ.ም ካደረገበት ማግሥት ጀምሮ፤ የአእላፋት ዝማሬን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ በብፁዓን አበውና በምእመናን በተሠጠው ‘የአእላፋት ዝማሬ መቀጠል አለበት’ የሚል አደራ ምክንያት የአእላፋት ዝማሬን የተመለከቱ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት በገና ዋዜማ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚካሔደውን ዓመታዊ የዝማሬ ሁነት በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የቅጂና ተዛማጅ መብቶች፤ "የአእላፋት ዝማሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሊካሔድ የሚችልና የባለቤትነት መብቱም የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ሆኖ መመዝገቡን" አዘጋጆቹ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የ2017 ዓ.ም የአእላፋት ዝማሬ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ በተመሳሳይ ሰዓት የሚካሔድ ሲሆን፤ ላለፉት ስምንት ወራት ለዚህ ታላቅ የዝማሬ ጉባኤ ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የዝማሬ መረሀግብሩ የሚካሔደውም በአዲስ አበባ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም እንዲሁም፤ በድሬዳዋ ለገሀር አደባባይ ብቻ መሆኑም ተገልጿል።
የአእላፋት ዝማሬ ዋነኛ ዓላማ ምእመናን ልደቱን ‘በባለ ልደቱ ቤት’ በዝማሬ እንዲያከብሩ ለማድረግ መሆኑን የገለጹት አዘጋጆቹ፤ በዚህ ዕለት የአእላፋት ዝማሬ’ ሥሙ እንደሚያሳየው አእላፋትን የሚያሳትፍ ዝግጅት በመሆኑ በከተማ ደረጃ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተባርኮ እንዲደረግና የአንድን ከተማ ሕዝብ በነቂስ ማሳተፍ በሚችል ደረጃ እንዲከናወን የታሰበ ዝግጅት መሆኑ አስታውቀዋል።
የአእላፋት ዝማሬ በEOTC ቴሌቪዥን አንዲሁም፣ በሀገሬና በአርትስ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሲሆን፤ ከአምስት በላይ ዓለም አቀፍ ሚድያዎችና ወደ ሰባት የሚጠጉ ሀገር አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሥፍራው ተገኝተው ለመዘገብ ፍቃድ መውሰዳቸው ተነግሯል።
በዚህ ምክንያት በአዲስ አበባው የአእላፋት ዝማሬ 60 '9ላይናሬ ስፒከር እና 10 ሞንታርቮዎች አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሲሆን፤ በድምፅ መሐንዲሶች ከፍተኛ ጥረት መድረክ ላይ የሚሰማው ድምፅና ከሩቅ የሚሰማው ድምፅ እኩል እንዲሆን ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁንም አክለዋል፡፡