ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አውሲ ረሲ ዞን፤ ኤሊዳር ወረዳ፣ ሲያራ ቀበሌ በጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 8 ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ ለአሐዱ አስታውቋል።

የአፋር ክልል ፖሊስ የማህበረሰብ አቀፍ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዋና ሳጅን ዋሱ ናስር በጥቃቱ የ8 ሰዎች ሕይወት ማለፋን የገለጹ ሲሆን፤ በተጨማሪም ሌሎች አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

የጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በዱብቲ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በጅቡቲ ድሮን እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ "በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ የድሮን ልምምድ አድርጓል" ብለዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን፤ በአካባቢው አርሶ አደሮች፣ ሴቶችና ሕጻናት ላይ የሞትና ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል

የጅቡቲ መንግሥት መከላከያ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ የድሮን ጥቃቱን መፈፀሙን በማመን በጥቃቱም 8 ሰዎችን መግደሉንም አስታውቋል።

በመግለጫው "የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው በራሳችን ግዛት ውስጥ ነው" ያለም ሲሆን፤ ጥቃቱ አሸባሪዎችን ለመምታት የተሰነዘረ መሆኑን ገልጿል።

በጉዳዩ ዙሪያ በፌደራል መንግሥት በኩል እስከአሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ