ጥር 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በግምት 100 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች በኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ተይዘው የመድኃኒት ክትትል ሳያደርጉ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚታሰብ በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ዴስክ ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

አሐዱም "እነዚህ ዜጎች የቫይረሱን ስርጭት እንዳያባብሱ እንደ ተቋም የመድኃኒት ክትትል እንዲያደርጉ በማፈላለግ ረገድ ምን እየሰራችሁ ነው?" ሲል በጤና ሚኒስቴር የኤች አይቭ ኤድስ የመከላከል ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አብነት አሰፋን ጠይቋል፡፡

ኃላፊዋ በምላሻቸው እነዚህን ዜጎች በስፋት የት ነው የሚገኙት በሚል እቅድ በመንደፍ፤ ከፍተኛ የማህበረሰብ ክፍል የሆኑት ተለይተው በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተረደገ ጥናትም መድኃኒቱን ከማይወስዱት ውስጥ በአብዛኛው ወይንም 18 በመቶ የሚሆኑት በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

"ይህንን የምርምር ጥናት ለማድረግ መነሻ የሆነውም 'በሀገር አቀፍ ደረጃ 605 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች በኤች አይቪ ቫይረስ ተይዘዋል' ተብሎ ምዝገባ ቢደረግም፤ አሁን ባለው ሁኔታ 500 ሺሕ የሚደርሱ ብቻ ናቸው የመድኃኒት ክትትል እያደረጉ ያሉት" ሲሉ ወ/ሮ አብነት ተናግረዋል፡፡

እንደ ተቋም በተደረገ ጥናት በአፍላ ወጣት ሴቶች ላይ የበሽታው ስርጭት ወደ 3 ነጥብ 7 መድረሱን ተከትሎ፤ ይህን ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡

"ለዚህ ሥርጭት መጨመር ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሴቶች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ክስተቶች ተጋላጭ ስለሆኑ ነው" ሲሉም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

"ምንም እንኳን በቫይረሱ የተያዙ ዜጎችን የመለየት ሂደቱ ፈታኝ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ 94 በመቶ በቫይረሱ የተያዙ ዜጎችን ክትትል ተደርጎ መድኃኒታቸውን በአግባቡ እየወሰዱ ነው" ያሉት ኃላፊዋ፤ "ከዚህ ውጭ የሆኑ ዜጎችም በቫይረሱ ተጠቂ ሆነው ራሳቸን ከመደበቅ ይልቅ የመደኃኒት ክትትል ማድረግ አለባቸው" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ