ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኮንጎ ጦር ከኤም 23 ታጣቂ ቡድን ጋር ባደረገው ውጊያ አራት ተጨማሪ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች መገደላቸው ተነግሯል።

ወታደሮቹ የተገደሉት በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሀገሪቱ ጦር ከኤም 23 ታጣቂ ቡድን ጋር በቀጠለው ውጊያ ነው ተብሏል።

ባለፈው ሰኞ በጎማ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ በተካሄደው ጦርነት ሦስት ወታደሮች ሲገደሉ፤ አንድ ሌላ ደግሞ ቀደም ሲል በተደረገው ጦርነት ቆስሎ መሞቱን የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ባወጣው በመግለጫው አስታውቋል።

መከላከያ ሠራዊቱ አርብ ዕለት ከኤም 23 ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ሁለት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ሃይል አባላትን ጨምሮ ዘጠኝ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች መገደላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።

በሩዋንዳ መንግሥት የሚደገፈው ኤም 23 በማዕድን የበለጸገውን ሰፊ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ክፍል እንዲሁም በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የክቡ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ የሆችውን ጎማን መቆጣጡን ተከትሎ፤ በተቀሰቀሰው አመፅ የአሜሪካና የኬኒያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ኤምባሲዎች ላይ ከባድ ጥቃት ተፈጽሟል።

Post image

በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሻሳ የሩዋንዳን ጨምሮ የበርካታ ምዕራባውያን እና አፍሪካ ኤምባሲዎች ውጭ ላይ ተቃዋሚዎች ተሰብስበው ኤምባሲዎችን በእሳት አቃጥለዋል።

በተጨማሪም የፈረንሳይ ኤምባሲ ላይ በተቃዋሚዎች ጥቃት መድረሱን የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሲኤንኤን ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚዎች ወደ ኤምባሲው መግባት አልቻሉም ብሏል፡፡

በትናንትናው ዕለት በኪንሻሳ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ፤ የአሜሪካ ዜጎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ መክሯል።

በዚህም "በኪንሻሳ ከተማ እየደረሰ ያለው ሁከት እየጨመረ በመምጣቱ በከተማዋ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ወደ መጠለያ ቦታ እንዲገቡ" ያሳሰበ ሲሆን፤ የተለያዩ አማራጮች ሲገኙ ከአገሪቱ እንደሚወጡ ገልጿል፡፡

Post image

ኤም 23 አማጺ ቡድን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ጎማ ከተማ ላይ የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲያቆም የዓለም ማህበረሰብ ጥሪ ቢቀርብለትም፤ አሁንም ጦርነቱ መቀጠሉ ነው የተገለጸው።

ሞስኮ በበኩሏ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ግጭት እንዲቆምና ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቅርባለች።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ