የፆታ ተኮር ጥቃት አድራሾች በብዛት የተጠቂዎች የቅርብ ሰዎች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም የትዳር አጋሮች በቀዳሚነት የጥቃቱ አድራሽ ሆነው ይታያሉ ብሏል።

የሕግ ማሻሻያዎችን በማደረግ እና ለተጎጂዎች ድጋፍ በመስጠት በቅርብ አጋሮች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ማስቆም የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ ስለመሆኑም ህብረቱ ጠቁሟል።

የፆታ ጥቃት አካላዊ ብቻ አለመሆኑም ያመላከተም ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ 13 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶች ደርሶባቸዋል ብሏል።

"ይህም ስድብ፣ ማስፈራራት እና አምባገነናዊ ተቆጣጣሪነትን ይጨምራል" ያለው ህብረቱ፤ በሰሃራ ዙሪያ ባሉ የአፍሪካ አካባቢዎች ደግሞ ወደ 29 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ እንደሚል አስታውቋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስር ሴቶች አንዷ አካላዊ ጥቃት እንደሚደርስባት ያስታወቀ ሲሆን፤ በመላው አፍሪካ ደግሞ ቁጥሩ ወደ አንድ ሦስተኛ የቀረበ መሆኑን ገልጿል።

"አላማ ተኮር የሆኑ ጣልቃ ገብነቶች ደግሞ ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ መልስ ለመስጠት እንዲሁም፤ ወደፊት ሁሉም ሰው በተሻለ ደህንነትና እኩልነት የሚኖርበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቁልፍ ድርሻ አለው" ሲል አክሏል።

በተለይም በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የህብረተሰብ ክፍል ውሰጥ የሚኖሩ ሴቶች ለፆታ ተኮር ጥቃት የበለጠ ተጋላጭ ሲሆኑ፤ "ከእነዚህም ውስጥ 11 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል" ብሏል።

በአንፃሩ ይህ ቁጥር ከፍተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ወደ 8 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ይላል ያለው የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ፤ ለሴቶች የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ጥቃትን ለመቀነስ የሚረዳ ስለመሆኑም ገልጿል፡፡