መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአበባ ምርት ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ 80 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ተሳታፊ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የግብርና ኢቨንስትመትና ምርት ገበያ ትስስር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ አበበ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ይህ የሆነው ደግሞ ሴቶች በአበባ ምርት ላይ ያላቸው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ነው፡፡
አሐዱ "ሴቶች በግብርና ዘርፍ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ምን ያህል ነው? በተለየ መልኩ በየትኛው የግብርናው ዘርፍ ላይስ ተሳትፏቸው የላቀ ነው?" ሲል አቶ ደረጄን ጠይቋል።
መሪ ሥራ አስፈፃሚው በሰጡት ምላሽ፤ "እንደ ሀገር ሲታይ በአበባ ምርት ላይ የሴቶች ተሳትፎ እጁጉን ለዉጥ የታየበት ዘርፍ ነው" ብለዋል።
ነገር ግን በግብርናዉ ዘርፍ ላይ የሴቶች ተሳትፎ በቂ ነው ማለት እንደማይቻል የገለጹት መሪ ሥራ አስፈፃሚዉ፤ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ከላይኛው ማዋቅር ወርዶ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተዋል።
"ይህን ደግሞ እውን ማድረግ የሚቻለው የግብርናውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ ሆኖ በቂ የሆነ መረጃ እንዲደርሳቸዉ ማድረግ ሲቻል ነው" ሲሉም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በግብርና ዘርፍ ላይ ሲታይ ወንዶች የበላይነቱን ይዘው እንደሚገኙ ያነሱት መሪ ሥራ አስፈፃሚዉ፤ "ነገር ግን ለሌሎች ሞዴል የሚሆኑ ሴት ኢንቨስተሮች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል" ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ የአበባ ምርት ኢንቨስትመንት ላይ 80 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ተሳታፊ መሆናቸው ተገለጸ
