መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ የተሰኘው የጥናትና ምርምር ተቋም የ2023 እና 24 የወጣቶች ሕይወት ዳሰሳ ጥናቱን በአዲስ አበባ እና በአምስት ክልሎች ያከናወነ ሲሆን፤ በጥናት ውጤቱም በአመጋገብ፣ በምግብ ዋስትና እና በአእምሮ ጤና ላይ አሳሳቢ አዝማሚያዎች መታየታቸውን አስታውቋል።
የተቋሙ ጥናት በትምህርት፣ በጤና እና ደህንነት እንዲሁም በሥራና በቤተሰብ ሕይወት ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ የሚዳስስ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በዚህም ጥናት በኢትዮጵያ ከክብደት በታች ያሉ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢሄድም፤ አሁንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
በተለይ 'ግጭት በተከሰተባቸው ክልሎች የምግብ ዋስትና እጦት በከፍተኛ ደረጃ ቀጥሏል' የተባለ ሲሆን፤ ከ10 ቤተሰቦች መካከል ሰባቱ በተወሰነ ደረጃ የምግብ ዋስትና እጦት አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
የያንግ ላይቭስ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አሉላ ፓንክረስት፤ "ግጭቶች በወጣቶች ላይ የሚያሳድሩትን ጎጂ ተፅዕኖ ያሳያሉ" ብለዋል።
"በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤና ስጋቶች ተባብሰዋል" ያለው ተቋሙ፤ ከአምስት ወጣቶች አንዱ ከጭንቀት ወይም ከድብርት ጋር የሚዛመዱ ምልክቶች እንደሚያሳይ አመላክቷል።
በግጭት ከተጎዱ ክልሎች በተለይም ከትግራይ እና ከአማራ የተውጣጡ ተሳታፊዎች የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የምግብ ዋስትና እጦት እና የአእምሮ ጤና መጓደል ጉዳቱን እንዳባባሰው መግለጻቸውም ተነግሯል።
እነዚህ ግኝቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ ፖሊሲዎች አስፈላጊነትን እንደሚያስፈልጉም ተቋሙ ባወጣው የወጣቶች ሕይወት ዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ የወጣቶች የአእምሮ ጤና ስጋቶች መባባሳቸውን ያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ አስታወቀ
