መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በሚከናወኑ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የሴቶች መሬትን በባለቤትንነት የመጠቀም መብት አነስተኛ መሆኑን ሃቢታት ፎር ሂውማኒቲ ኢትዮጵያ አስታውቋል
ተቋሙ ኢንቨስትመንት በሴቶች የመሬት መብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ አጽንኦት በመስጠት ጥልቅ ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ ኢትዮጵያ ፖሊሲ አድቮኬሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ አደም አሎ፤ "ሴቶች የመሬት መብታቸውን ለማስከበር፣ ለዘላቂ ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል ፍትሃዊ እና ፍትሃዊ አካባቢ ለመፍጠር የጋራ ርብርብ ወሳኝ ነው" ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰር መለሰ ዳምጤ በበኩላቸው፤ የሴቶች መሬት የማግኘትና የመጠቀም መብት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የተደነገገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ይሁን እንጂ ባህላዊ ወጎች ሴቶች መሬት እንዳይጠቀሙ ይከለክላሉ" ያሉት ፕሮፌሰር መለሰ፤ "የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብትን ማረጋገጥ ሕይወታቸውን ከማስተካከሉም በላይ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ልማት ያላቸው አስተዋጽኦ የጎላ ያደርገዋል" ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መጠነ ሰፊ የመሬት ኢንቨስትመንቶች በሴቶች የመሬት መብት ላይ የሚያደርሱትን አወንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች የተሻሻለ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
አክለውም፤ "ከባለድርሻ አካላት እና ከስልታዊ አጋሮች ጋር የተሻሻለ ግንኙነት በመፍጠር በሴቶች የመሬት መብት ላይ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ጥብቅና ግንዛቤን ማሳደግ ያስፈልጋል" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩም የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም ፍትሃዊ የመሬት አጠቃቀምን እና አስተዳደርን በትልልቅ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያካትቱ እድሎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ