መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ ዞን ከሰሞኑ ምንነቱ ያልታወቀ እና በአካባቢው የሚገኙ እንሰሳትን እያጠቃ ያለ አዲስ የእንሰሳት በሽታ መከሰቱን ተከትሎ፤ በሽታው በላብራቶሪ እየታየ ፍተሻ እየተደረገበት እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ ለአሐዱ አስታውቋል።

በሽታው በአንድ ከተማ አስተዳደርና በሦስት ወረዳዎች የተከሰተ ሲሆን፤ በተለይም ካምባ እና ገረሴ በሚባሉ ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ከብቶች በዚህ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ በፍጥነት እየተጠቁ ስለመሆናቸው የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ስመኝሽ አጩራ ተናግረዋል።

የበሽታው ምንነት ላይ የተደረሰበት ማረጋገጫ ባይኖርም፤ የክረምት ወቅትን ተከትለው የሚመጡ የተለመዱ የእንሰሳት በሽታዎች በመኖራቸው እነሱን በየወረዳው ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

በሽታዉ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን እና አስጊ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር እየተሰራ ስለመሆኑም ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በዚህም የአባ ሰንጋ፣ አባ ጎር፣ ጎሮርሳ እና ሌሎችም በዝናብ ወቅት የሚከሰቱ ወረርሽኞች ለመከላከል የክትባት እጥረት ዞኑ ገጠሞት የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ መሻሻሎች ስለመኖራቸው እና አዲስ ስለተከሰተው በሽታም በላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

አክለውም አሁን ላይ ይህ በሽታ ለጊዜው በዞኑ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ላይ በመከሰቱ፤ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች እንዳይዛመት የጥንቃቄ እና የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑ ለአሐዱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ