መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሁኑ ሰዓት በአይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን አካባቢ እንደሚደርሱ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት አስታውቋል።
በዚሁ ጉዳይ ከ16 ዓመት በፊት በተሰራ ጥናት 300 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ለአይነ ስውርነት ተጋላጭ መሆናቸው መረጋገጡን የገለጹት የአገልግሎቱ ም/ ዋና ዳይሬክተር ጤናዬ ደምሴ፤ አሁን ላይ የተጠናከረ ጥናት ቢደረግ ከዛም በላይ በርካታ ቁጥር ሊኖረው እንደሚችል ለአሐዱ ገልጸዋል።
ሆኖም ግን ያለውን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት በግምት በአማካኝ እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለአይነ ስውርነት ተጋልጠው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ ብቻ ይባል እንደነበረና በደንብ ቁጥር 528/2015 ተጨማሪ ኃላፊነቶችን በመያዝ፤ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት በሚል በመሻሻሉ ከዛን ጊዜ በኋላ የአይን ብሌን ልገሳን መሉ በመሉ እያስተባበረ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።
አክለውም የአይን ብሌን ጠባሳ ሕመም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አሳስበው፤ "ችግሩ በደንብ ያለ ቢሆንም ግን የማህበረሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ታክመው መዳን የሚችሉ በርካታ ዜጎች ለአይነ ስውርነት እየተጋለጡ ይገኛሉ" ብለዋል።
የአይን ብሌንን ለመለገስ ቃል የገባ ሰው ሕይወቱ ካለፈበት እስከ 8 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ንቅለ ተከላው መከናወን እንደሚገባው ያነሱም ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ ግን የእድሜ ገደብ እንደማይወስነውና የማንኛውም ሰው ለሁሉም አይን እንደሚሆን ተመላክቷል።
በመሆኑም "ማንኛውም ሰው ከሞተ በኋላ የአይን ብሌኑን ለሰዎች ለመስጠት ቃል በመግባት ለብዙዎች ብርሃን በመሆን በዚህ ችግር የሚሰቃዩ ወገኖችን መታደግ ይገባዋል" ሲሉ ም/ ዋና ዳይሬክተሯ አፅንኦት ሰጥተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ በአይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ለአይነ ስውርነት መጋለጣቸው ተነገረ
