ጥር 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የስንዴ ዱቄት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚያመርቱት ምርት ውስጥ የተለያዩ በቫይታሚን እና በማዕድን የበለጸጉ ግብዓቶችን በመጨመር እንዲያመርቱ የሚያስገድድ ሕግ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የአምራች ኢንዱሰትሪ ምርምር እና ልማት ማዕከል የምግብ እና መጠጥ ልማት ማዕከል ተመራማሪ ፍቅሩ አበበ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ፎሊክ አሲድን ጨምሮ ቫይታሚን ቢ ኮምፕሌክስ፣ ቫይታሚን ዲ፤ ዚንክ እንዲሁም ሌሎች የቫይታሚን እና የማዕድን አይነቶችን የስንዴ ዱቄት ምርታቸው ላይ በመጨመር የማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ እየተደረ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

አሐዱም "ከስንዴ ውጪ ሁሉም ማህበረሰብ የሚጠቀማቸውን የምግብ ግብዓቶች ላይ ለምን ተጨምሮ የሚሰራበት አካሂድ የለም ወይ?" ሲል አቶ ፍቅሩን ጠይቋል፡፡

በምላሻቸውም ስንዴ 37 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ እንደሚጠቀመው በማስታወስ፤ "በሌሎች ግብዓቶች ላይ መጠቀም ያልተቻለው የምርት ሂደታቸው ማዕድኖች እና ቫይታሚኖችን ለመጨመር አስቸጋሪ መሆኑን ነው" ብለዋል፡፡

እንደ ምሳሌነትም የጤፍ አመራረት እና ወደ ዱቄት የሚቀየርበት አካሄድ ለአሰራር እንደማይጋብዝ ተናግረዋል፡፡

የስንዴ ዱቄት አምራቾች ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ምርቶች ላይም መሰል ተግባራት እንደሚሰሩና የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ