ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባዔ የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሁለት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከምክር ቤቱ በርካታ ሀሳቦች የተነሱበት ሲሆን፤ ከእነዚህም ሕገወጥ የነዳጅ ንግድ እና ግብይትን በተመለከተ ስለሚወሰዱ የእርምት እና የቅጣት ደንቦችን ጨምሮ የነዳጅ አቅርቦትን በኢትዮጵያ ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እና ሌሎችን ጉዳዮች በተመለከት የምክር ቤት አባላት አስተያየቶች ሰጥተዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ከ 500 በላይ ወረዳዎች የነዳጅ ማደያዎች እንደሌላቸዉ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህንን የተደራሽነት ችግር ለማስቀረት የታለመ ደንብ በአዋጁ መካተቱ ተገልጻል።
ሕገወጥ የነዳጅ ማደያ ግንባታና ከታሪፍ በላይ ንግድ መስፋፋቱን ተከትሎ አዋጁ የሚያስተካክለዉ የሕግ ማዕቀፍ ስለመኖሩም ተገልጿል።
በተጨማሪም መንግሥት ከሚያወጣው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ተመን ውጪ በተደጋጋሚ የመገበያየት ወንጀል እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል፤ ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ከ300 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር ቅጣት እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጭ ያከማቸ፣ በዚህም ሊሸጥ ከሚገባው ሰው ቦታና የግብይት ስርዓት ውጭ ሲሸጥ የተገኘ ወይም አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ፤ የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስርና ከ350 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚቀጣ በአዋጁ ተካቷል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባዔው የም/ቤቱ 13 መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ በሙሉ ድምጽ የፀደቀ ሲሆን፤ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅንም እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።