ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት ከ514 ሺሕ 319 ኩንታል በላይ የሚሆን የሰብል ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አስታውቋል።

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ሰብሉ ላይ አደጋ መድረሱን የገለጸው ጽ/ቤቱ፤ በተለይ በዝናብ እጥረት፣ በበረዶ፣ በጎርፍ እና በተባይ በሽታ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም በተባይ በሽታ 34 ሺሕ 740 ኩንታል፣ በበረዶ 28 ሺሕ 194 ኩንታል እንዲሁም፤ በዝናብ እጥረት 421 ሺሕ 100 ኩንታል ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ጽ/ቤቱ ለአሐዱ በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

Post image

በተጨማሪም በጎርፍ 3 ሺሕ 252 እና በተለያዩ በሽታዎች ደግሞ 27 ሺሕ 32 ኩንታል በሚሆን የሰብል ምርት ላይ ጉዳት መድረሱን አክሎ አንስቷል፡፡

በአጠቃላይ በዞኑ ከ2015 ጀምሮ እስከ አሁን በያዝነው የምርት ዘመን 514 ሺሕ 320 ኩንታል የሚሆን የሰብል ምርት ላይ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም ማህበረሰቡ እንዳይጎዳ በሚል ከሚመለከተው አካል በጋራ በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ያመላከተው መረጃው፤ ነገር ግን እስከ አሁን ባለው ጊዜ በበቂ ሁኔታ የድጋፍ አይነቶች እየደረሱ ነው ለማለት ያስቸግራል ብሏል፡፡

ምክንያቱም ባለው ነባራዊ ሁኔታ በታቀደውና በታሰበው ልክ እርዳታዎችን ተደራሽ ለማድረግ አለመቻሉን ገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ