ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የ1446 ኛው የሐጅ እና ዑምራ ጉዞ ምዝገባ ከጥር 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 21 በሁሉም አካባቢዎች እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የዘንድሮውን የሐጅና ዑምራ ጉዞ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የ1446 ኛው የሐጅ እና ዑምራ ጉዞ ምዝገባ ከጥር 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ድረስ በሁሉም የክልል እና የከተማ አስተዳደር የምዝገባ ጣቢያዎች እንደሚከናወን አታውቋል፡፡

Post image

የሳውዲ አረቢያ የሐጅ ሚኒስቴር ምዝገባው ከየካቲት 21 ቀን 2017 በፊት እንዲጠናቀቅ ግዴታን ማስቀመጡን ተከትሎ፤ ሁጃጆች (ተጓዦች) ቀድመው የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያጠናቅቁ ተጠይቋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የዘንድሮ የሀጅ እና ዑምራ የጉዞ ዋጋ 625 ሺሕ ብር መሆኑንም ያስታወቀ ሲሆን፤ ለዋጋ ጭማሪውም የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የታየው የዶላር ጭማሪና በአየር መንገዶች ላይ ያለው የትኬት ዋጋ መናር እንደምክንያት ተገልጿል።

የአገልግሎት ዋጋን በመቀነስ በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በማጠፍና በሳውዲ የሚቀርበውን አገልግሎት ተመጣጣኝ እንዲሆን በማድረግ 108 ሺሕ ብር ቅናሽ እንዲኖረው ማድረጉንም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

ምዝገባው አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 30 የምዝገባ ጣቢያዎች የሚካሄድ ሲሆን፤ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሁሉ በቀነ ገደቡ እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀርቧል።

በዘንድሮው የሐጅ ጉዞ ለ10 ሺሕ ተጓዦች መፈቀዱ በመግለጫው የተነገረ ሲሆን፤ ተጓዦች ለምዝገባ ሲመጡ የቀበሌ መታወቂያና የታደሠ ፓስፖርት ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ